የአፍሪካን የውሃ ሃብት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማስፈን የአህጉሪቷን ዕድገት ማሳለጥ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን የውሃ ሃብት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማስፈን የአህጉሪቷን ዕድገት ማሳለጥ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦የአፍሪካን የውሃ ሃብት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማስፈን የአህጉሪቷን ዕድገት ማሳለጥ እንደሚያስፈልግ የሌሴቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ማኩጆ ገለጹ።
48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል።
በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የአንጎላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሳቢ ሊቀ መንበር አምባሳደር ቴቴ አንቶኒዮ እና የአባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተሳትፈዋል።
በመደበኛ ስብሰባው የተሳተፉት የሌሴቶ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ማኩጆ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሌሴቶ በደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና ዜጎችን በንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነት ማስተሳሰር የሚያስችል አቅም አላት።
የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ በዘላቂ ውሃ ልማትና ንጽህና አጠባበቅ ላይ ትኩረት ማድረጉ የውሃ ሃብት አስተዳደርና ተደራሽነትን በማስፋት አጀንዳ 2063 እውን ለማድረግ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
የሌሶቶ ዋና ዋና ወንዞችም ለደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና፣ ናሚቢያና ሌሎች የደቡብ አፍሪካ ቀጣና ሀገራት የንጹህ መጠጥ ውሃ የማቅረብ አቅም ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም በአፍሪካ ሕብረት የ2026 የውሃና የንፅህና አጠባበቅ በተቀመጠው መሪ ሃሳብ መሰረት ከቀጣናው ሀገራትና ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አንስተዋል።
ሌሴቶ ለቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብር መጠናከር በቁርጠኝነት የምትሰራ ሀገር መሆኗን አስረድተዋል።
ለዚህም የሁሉም ድምጽ በፍትሐዊነት የሚሰማበት ጠንካራ የባለብዙ ወገን ሥርዓት ለማጎልበት በቅንጅት እየሰራች መሆኗን አብራርተዋል።
የአፍሪካ የውሃ ሃብት ለአህጉሪቷ ዕድገት ወሳኝ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም የአፍሪካን የውሃ ሃብት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማስፈን የአህጉሪቷን ዕድገት ማሳለጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል ።