የጨቅላ ህጻናት ''የገላ ለገላ ክብካቤ ዘዴ'' የጨቅላ ህጻናት ሞት በ50 በመቶ እንዲቀንስ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የጨቅላ ህጻናት ''የገላ ለገላ ክብካቤ ዘዴ'' የጨቅላ ህጻናት ሞት በ50 በመቶ እንዲቀንስ አስችሏል
ሀዋሳ፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል በሙከራ ደረጃ በተተገበረው ወዲያውኑ የሚሰጥ የጨቅላ ህጻናት ''የገላ ለገላ ክብካቤ ዘዴ'' የጨቅላ ህጻናት ሞት በ50 በመቶ መቀነሱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሲዳማ ክልል በሙከራ ደረጃ የተተገበረው ''ወዲያውኑ የሚሰጥ የጨቅላ ህጻናት ገላ ለገላ ክብካቤ ዘዴ'' የማስተዋወቂያ ሀገር አቀፍ መድረክና የመስክ ምልከታ በሃዋሳ ተካሄዷል።
''ወዲያውኑ የሚሰጥ የጨቅላ ህጻናት ''የገላ ለገላ ክብካቤ ዘዴ'' እድሜያቸው ሳይደርስና በአነስተኛ ኪሎ ለሚወለዱ ህጻናት የሚሰጥ የህክምና አገልግሎት ነው።
ይህም በሲዳማ ክልል በሙከራ ደረጃ ተተግብሮ ውጤታማ በመሆኑ በመላ ሃገሪቱ እንዲስፋፋ ዛሬ ይፋ ተደርጓል።
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ መንግስት የእናቶችና ጨቅላ ህጻናትን ጤና ለማሻሻል ያከናወናቸው ተግባራት ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል።
ለዚህም የጤና ተቋማትን የማስፋፋትና የህክምና ቁሳቁስ የማሟላት፣ በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር የማሳደግ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
የሙከራ ትግበራ በተደረገባቸው ሆስፒታሎች የጨቅላ ህጻናትን ሞት እስከ 50 በመቶ መቀነስ መቻሉን በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል።
የሙከራ ትግበራው ህጻናትና እናቶችን አንድ ላይ ለማከም የሚያስችል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ይህንንም በመላ ሃገሪቱ ተግባራዊ በማድረግ በ2030 የጨቅላ ህጻናት ሞትን ለመቀነስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ በበኩላቸው፤ ወዲያው የሚሰጥ የጨቅላ ህጻናት ''የገላ ለገላ ክብካቤ ዘዴ'' በክልሉ በሙከራ ደረጃ ተተገብሮ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጨቅላ ህጻናት ህክምና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ተፈጥሯዊ በሆነ ዘዴ ከእናት ጋር በሚደረግ የገላ ለገላ ንክኪ ያለጊዜያቸው የሚወለዱና አነስተኛ ኪሎ ያላቸው ህጻናትን ከሞት መታደግ ተችሏል ብለዋል፡፡
ለስራው ውጤታማነት የተቋማት፣ የባለሙያና የማህበረሰቡ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሰላማዊት ተሞክሮውን ለማስፋት ቅንጅታዊ ስራን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የትግበራው ውጤታማነት ጥናት በሲዳማ ክልል በሚገኙ አራት ሆስፒታሎች መተግበሩን የገለጹት ደግሞ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈጻሚና ወዲያው የሚሰጥ የጨቅላ ህጻናት ''የገላ ለገላ ክብካቤ ዘዴ'' የሙከራ ትግበራ ጥናት አስተባባሪ ዶክተር ፍጹም ወልደገብርኤል ናቸው።
ጥናቱ በተለይ በ28 ቀናት ውስጥ የሚኖረውን የጨቅላ ህጻናት ሞት ምጣኔ ለመቀነስ የሚያስችልና የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ እንደ ሃገር በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቱላ አጠቃላይ ሆስፒታል በጨቅላ ህጻናትና እናቶች ሕክምና ክፍል ያገኘናቸው ወይዘሮ ጸሃይ ተስፋዬ ፤ አነስተኛ ክብደት ያለው ህጻን በመውለዳቸው ወዲያውኑ የሚሰጥ የጨቅላ ህጻናት ''የገላ ለገላ ክብካቤ ዘዴ'' ማእከል መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
በማእከሉ በባለሙያዎች በተደረገላቸው እገዛ ልጃቸውን እንደወለዱና ባደረጉት ''የገላ ለገላ ክብካቤ ዘዴ'' ህጻኑ ጡት መጥባት እንደጀመረና ክብደቱም እንደጨመረ ተናግረዋል፡፡
በሙከራ ትግበራው ይፋ ማድረጊያ መርሃ ግብር ላይ ከሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎችና የሚኒስቴሩ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ትግበራው በተደረገባቸው ሆስፒታሎች የመስክ ምልከታና ውይይት ተደርጓል፡፡