በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረጉ የልማት ኢኒሼቲቮች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ጀምረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረጉ የልማት ኢኒሼቲቮች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ጀምረዋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረጉ የልማት ኢኒሼቲቮች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መጀመራቸውን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ እና የመንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን ማጠቃለያ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሱፐርቪዥን ቡድኑ አባላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይ የሱፐርቪዥን አባላቱ በክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ባደረጉት ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን ያገኟቸውን ውጤቶችና ተሞክሮዎች አቅርበዋል።
በዚህም መንግስት ተግባራዊ ያደረጋቸው የልማት ኢኒሼቲቮች የሕዝብን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይም ተረጂነትን ለማስቀረት፣ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ በልማት ስራዎች፣ በግብርና ልማት፣ በኮሪደር ልማት፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግር እና ከኢንዱትሪያላይዜሽን እንዲሁም ከሌሎች አኳያ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸው ተጠቅሷል።
በዚህ ወቅት የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ እንደተናገሩት፤ የዚህ ሱፐርቪዥን ዋነኛ ዓላማ በከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ማጠቃለያ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎችና የሥራ መመሪያዎች አፈጻጸም መገምገም ነው።
"በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሀሳብ በተሰጠው ስልጠና ማጠናቀቂያ ላይ ሀገራዊ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ የተሰጡ ዝርዝር መመሪያዎች መሬት ላይ የወረዱበትን ሁኔታ ሱፐርቪዥኑ በዝርዝር መመልከቱንም ተናግረዋል።
በዚህም በክልሎችና በሁለቱም የከተማ አስተዳደሮች በተደረገው ምልከታ፤ መንግሥት ተግባራዊ ያደረጋቸው የልማት ኢኒሼቲቮች የሕዝብ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑ መታየታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ተረጂነትን ለማስቀረት፣ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የተጀመሩ ጥረቶች፣ በግብርና፣ በኮሪደር ልማትና በኢንዱስትሪያላይዜሽን ዘርፎች የታዩ ውጤታማ ሥራዎች፣ ከቴክኖሎጂ ሽግግርና ከሌሎች የልማት ስራዎች አኳያ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የሱፐርቪዥን ቡድኑ የተሰጠውን ተልዕኮ በውጤታማነት ማከናወኑን ጠቅሰው፤ ስራዎች ከዕቅድ ባለፈ በተግባር መሬት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መጀመራቸው የታየበት ትልቅ ግብዓት የተገኘበት ሂደት መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ በክልሎች መካከል የሚታየውን የአፈጻጸም ልዩነት ለማቀራረብና ተመሣሣይ ውጤት እንዲመዘገብ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የአፈጻጸም ልዩነትን ለማቀራረብ ሦስት ዋና ዋና ስልቶች እንደሚተገበሩ ጠቁመዋል።
በዚህም ለጉዳዮች ባለቤት የማበጀት ተግባር እንደሚከናወን ጠቁመው፤ ተቋማት እንደየሥራ ባሕሪያቸው የወረዱ የልማት ኢኒሼቲቮችን ውጤታማነት የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዲወስዱ ይደረጋል ብለዋል።
የተቋማትን ቅንጅት ማጠናከርም ሌላኛው ስልት መሆኑን ጠቅሰው፤ በሁሉም ኢኒሼቲቮች ላይ የተናበበ አሰራር እንዲኖር እንደሚሰራ አብራርተዋል።
በተመሣሣይ ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትልን በማጠናከር አፈጻጸምን የመከታተል፣ ስታንዳርድ የማበጀትና ማነቆዎችን የመፍታት ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
በክልሎች ባላቸው ጸጋ ልክ ሥራዎችን እንዲተገብሩና የሕዝብን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ የክትትልና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል።