ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ደኅንነት ለአፍሪካ ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ በጤናው ዘርፍ የተመዘገበ ወሳኝ ስኬት ነው 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ደኅንነት የትውልዶችን የተመጣጠነ የምግብ እጥረት አዙሪት የሚሰብርና ለአፍሪካ ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ በጤናው ዘርፍ የተመዘገበ ስኬት መሆኑን የሌሶቶ ንጉሥ እና የአፍሪካ ሕብረት የሥርዓተ-ምግብ አምባሳደር ንጉስ ሌትሲ ሣልሳዊ ገለጹ።

የሌሶቶ ንጉሥ እና የአፍሪካ ሕብረት የሥርዓተ-ምግብ አምባሳደር ንጉስ ሌትሲ ሣልሳዊ በአዲስ አበባ የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል።


 

በጉብኝቱም የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የኒውትሬሽን ኢንተርናሽናል ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጆይል ስፓሰር እና የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ተገኝተዋል።

የንጉስ ሌትሲ ሣልሳዊ የዘውዲቱ ሆስፒታል ጉብኝትም በሆስፒታሉ በልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት እና በሥርዓተ ምግብ ደኅንነት የሚከናወኑ ተግባራትን ለመመልከት ያለመ መሆኑን ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ (ፒኦኤ) ዘግቧል።

የሌሶቶ ንጉሥና የአፍሪካ ሕብረት የሥርዓተ-ምግብ አምባሳደር ንጉስ ሌትሲ ሣልሳዊ÷ በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የእናቶችና ህፃናት አያያዝ የኢትዮጵያ ቁርጠኛ የጤና ፖሊሲ እርምጃን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በህፃናት ዕድገትና በእናቶች ጤና አጠባበቅ በፈጠራና በርህራሄ የተደገፈ የተቀናጀና አስተማሪ የጤና ሥርዓት እየገነባች መሆኑን በምልከታቸው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።


 

በዚህም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን፣ ጠንካራ የእናቶችና ህፃናት ጤና ሥርዓት፣ የተመጣጠነ የምግብና የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ውጤታማ አቅም እየፈጠረች መሆኗን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የእናቶችና ህፃናት ጤና አጠባበቅ ሥርዓት ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገርን የተመጣጠነ የምግብ እጥረት አዙሪት የሚሰብር ወሳኝ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ምልከታቸውም ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር በአርዓያነት የሚቀሰም አስተማሪ የእናቶችና ህፃናት ጤና እንክብካቤ ሥርዓት መፈጠሩን መመልከታቸውን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ተሞክሮም የፖለቲካ ቁርጠኝነት የታከለበት የሚጨበጥ የጤና አቅም እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ÷ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ አስተማማኝ የጤና ሥርዓት እየገነባች እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም መንግስት በወሰደው ቁርጠኛ አቋም በዜጎች የሥርዓተ ምግብ ደኅንነት፣ በእናቶችና ህፃናት ሞት ቅነሳ እመርታዊ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠንካራ የጤና ተቋማት ለመገንባትም በሁሉም ክልሎች ዘመናዊ ሆስፒታሎችን በመገንባት ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

የኒውትሬሽን ኢንተርናሽናል ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጆይል ስፓሰር÷ ዓለም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በቀላሉ መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች በርካታ ህፃናት ለህልፈት እንደሚዳረጉ ገልጸዋል።


 

በዚህም አፍሪካ የእናቶችና ህፃናትን ሞት መቀነስ የሚያስችል አስተማማኝ የሥርዓተ ምግብ አቅም መገንባት እንደሚኖርባት አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ አካታች የጤና ሥርዓት በመገንባት የእናቶችና ህፃናትን ሞት በመቀነስ ትርጉም ያለው የሥርዓተ ምግብ ደህንነት ለመገንባት አስደናቂ ሥራ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም