በከተማዋ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለፉት ስድስት ወራት 14 ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለፉት ስድስት ወራት 14 ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ገብተዋል
ባህር ዳር፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦በባህር ዳር ከተማ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 14 ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት መግባታቸውን የከተማዋ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።
የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የአስተዳደሩ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በባህር ዳር ከተማ ወደ ሥራ የገቡ ኢንዱስትሪዎችን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ብርሃን ንጉሴ፤ የ“ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” ንቅናቄ የከተማዋን የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ማነቃቃቱን ተናግረዋል።
ንቅናቄውን ተከትሎ ባለፉት ስድስት ወራት ለኢንዱስትሪዎች በተደረገ ድጋፍና ክትትል 14 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መግባታቸውን ገልጸዋል።
በባህር ዳር ከተማ 73 ነባርና አዲስ ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርት ላይ አተኩረው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢንዱስትሪዎቹ ባለፉት ስድስት ወራት ከ66 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ችለዋል ነው ያሉት።
በከተማዋ አራት ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ወደ ውጪ በመላክ ከ3 ነጥብ 1ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማስገኘታቸውንም የመምሪያ ሃላፊዋ አመልክተዋል።
እንደሃላፊዋ ገለጻ፤የኢትዮጵያ ታምራት ንቅናቄ የከተማዋን የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከማነቃቃት በላይ ከ2 ሺህ 400 ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ አስችሏል።
በከተማዋ አጠቃላይ 273 ኢንዱስትሪዎች በማምረት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው መንግስት ለኢንዱስትሪዎቹ ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኤም.ኤስ.ሲ ቢዝነስ ግሩፕ የባህር ዳር ቀጣና ሥራ አስኪያጅ አበረ አበራ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ፋብሪካው በእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያና በምግብ ዘይት ማምረት ላይ ተሰማርቶ እየሰራ ይገኛል።
ፋብሪካው በቀን እስከ 200 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት የማምረት አቅም እንዳለውና በአሁኑ ወቅትም ተኪ ምርት በማምረት የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት በኩል የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
በከተማ አስተዳደሩ እየተደረገላቸው ያለው ክትትልና ድጋፍ የሚያስመሰግንና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ያሉት ደግሞ የአማጋ ባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አማረ መብራቴ ናቸው።