ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌትነቷን በአስደናቂ የልማት ጉዞ እየደገመችው ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ታሪክ፣ የልማት ጉዞ እና የእንግዳ ተቀባይነት እሴት ለአፍሪካውያን ትልቅ ትምህርት እና ኩራት መሆኑን ለአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ለመሳተፍ የመጡ እንግዶች ተናገሩ።

39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ በመጪው ቅዳሜና እሁድ ይካሄዳል።

ይህንን ተከትሎም የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና ሌሎችም እንግዶች ወደ አፍሪካ መዲና አዲስ አበባ በመግባት ላይ ናቸው።

በጉባዔው ለመሳተፍ አዲስ አበባ የገቡ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ወደ መዲናዋ ሲደርሱ የተደረገላቸው አቀባበል እጅግ የሚያስደንቅ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከካሜሩን የመጡት ሪጎ ባት ሲሎ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ የተደረገላቸው አቀባበልና መስተንግዶ አስደማሚ መሆኑን አንስተው፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ኩራትና የሉዓላዊነት ምልክት ነው ብለዋል።

አየር መንገዱ አፍሪካዊ ማንነትንና ብቃትን ለዓለም የሚያሳይ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ሌሎች አፍሪካን ከሚስሉበት አሉታዊ ገጽታ በተቃራኒ፣ አዲስ አበባ የአፍሪካን እውነተኛ የዕድገትና የዘመናዊነት ገጽታን ለዓለም እያሳየች መሆኗንም ጠቅሰዋል።

የዓድዋ ድል እኛ አፍሪካውያን በዚህ ዘመን በአፍሪካዊ መንገድ ራሳችንን ማሳደግ እንደሚገባንና የተሟላ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንዳለብን የሚያስተምር ዘመን አይሽሬ ታራክ መሆኑን አንስተዋል።


 

በጉባኤው ለመሳተፍ የመጣው የስዋቲኒ ልዑክ አባል ኪንታኒ ዶኩታኒ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የእንግዳ ተቀባይነት እና አብሮ የማደግ መንፈስ በመላው አህጉሪቱ ሊሰራጭ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአፍሪካውያን ማዕከል የሆነችው ኢትዮጵያ የአህጉሪቱን ጥቅም የምታስጠብቅ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለሌሎች አፍሪካውያን ዓይን ከፋች ስኬት መሆኑን በመጥቀስ፥ ኢትዮጵያውያን የዓድዋን ድል በልማት እየደገሙት ነው ብለዋል።

ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ ፈጣን የብዝኃ ዕድገት ሞዴል ልምድ በመቅሰም ለስኬት ሊተጉ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም