የተደረገልን የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ለተሻለ ሥራ የሚያነሳሳን ነው - አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የተደረገልን የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ለተሻለ ሥራ የሚያነሳሳን ነው - አርሶ አደሮች
ሮቤ ፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦በባሌ ዞን የተደረገላቸው የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ለተሻለ ሥራ እንደሚያነሳሳቸው ከግብርና ወደ ኢንቨስትመንት በመሸጋገር እውቅና ያገኙ አርሶ አደሮች ገለጹ።
በባሌ ዞን ከግብርና ወደ ኢንቨስትመንት ለተሸጋገሩ 301 አርሶ አደሮች እና ማህበራት የኢንቨስትመንት ፍቃድ መስጠቱንም የዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ገልጿል።
አርሶ አደር ኡመር አህመድ ባለፉት ዓመታት በተሰማሩበት የግብርና መስክ ውጤታማ በመሆን ወደ ኢንቨስትመንት ከተሸጋገሩ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
አርሶ አደሩ በስንዴና ሌሎች ሰብሎች ሽያጭ ውጤታማ በመሆን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር አስመዝግበው በዛሬው እለት ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን ነው የሚገልጹት።
በአሁኑ ወቅትም በግብርና የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ሶስት ሄክታር የኢንቨስትመንት መሬትን በማበረታቻነት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በተሰማሩበት የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና ሽያጭ ስራ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ካፒታል በማስመዝገብ ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን የገለጹት ደግሞ የደሎ መና ወረዳ አርሶ አደር አብዱልከሪም ኢብራሂም ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ከተሰጣቸው የእውቅና ሰርተፊኬት ባሻገር በኢንቨስትመንት ማበረታቻነት 10 ሄክታር የመሥሪያ ቦታ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ እንዳሉት የተደረገላቸው ዕውቅናና የኢንቨስትመንት ማበረታቻ መሬት በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የሚያነሳሳ ነው ይላሉ።
የዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ኢብሮ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በዞኑ 301 አርሶ አደሮች እና የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ከግብርና ወደ ኢንቨስትመንት ተሸጋግረዋል።
አርሶ አደሮቹና ኢንተርፕራይዞቹ ባለፉት ዓመታት በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ ከመሆን ባሻገር በነፍስ ወከፍ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ለማስመዝገብ እንደቻሉም ተናግረዋል።
ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩት አርሶ አደሮች ወደ ሥራ ሲገቡ ከ14 ሺህ 400 ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።
ወደ ኢንቨስትመንት ለተሸጋገሩ አርሶ አደሮች ከ1 ሺህ 202 ሄክታር የሚበልጥ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ የተሰጣቸው መሆኑን ነው ኃላፊው የተናገሩት።
ለአርሶ አደሮቹና ማህበራቱ በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ የመሬት አቅርቦትና ሌሎች ማበረታቻዎች እንደተደረገላቸው የገለጹት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ኃይሌ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ባከናወኑት ውጤታማ ሥራ ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩት ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች የግብርናው መስክ ሽግግር አዎንታዊ ማሳያዎች መሆናቸውን አክለዋል።
በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት የዛሬዎቹን ጨምሮ ከ437 የሚበልጡ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮችና ማህበራት ባስመዘገቡት ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸው ተመልክቷል።