ቀጥታ፡

የማቆያ ማዕከሉ የቅድመ ወሊድ ክትትል ዕድልን በመፍጠር የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ሞትን ለመቀነስ የማይተካ ሚና አለው

ሳውላ ፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሳውላ ጤና ጣቢያ የተገነባው የእናቶች ማቆያ ማዕከል የቅድመ ወሊድ ክትትል ዕድልን በመፍጠር የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ሞትን ለመቀነስ የማይተካ ሚና እንዳለው ተመላከተ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሳውላ ከተማ ጤና ጣቢያ የተገነባው የእናቶች ማቆያ ማዕከል ዛሬ ተመርቋል።


 

የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘላለም አበራ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለፁት፤ በሆስፒታሉ በ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የተገነባው የእናቶች ማቆያ ለነፍሰ ጡር እናቶች በቅርበት ክትትል ለማድረግ ትልቅ ጠቀሜታ አለው።


 

በገጠር የሚገኙ ነፍሰ ጡር እናቶችን በወሊድ ወቅት ወደ ጤና ጣቢያና ሆስፒታል ለማምጣትና የመንገድ መሰረተ ልማቱ ባልተሟሉባቸው አካባቢዎች ለእናቶች የወሊድ አገልግሎት ለመስጠት አዳጋች እንደነበር ጠቁመዋል።

በዚህ ሁኔታ በእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ላይ የሚያጋጥመውን ጉዳት ለመቀነስ እናቶች በጤና ጣቢያ ውስጥ በመቆየት የቅድመ ወሊድ ክትትል የሚያደርጉበት ማቆያ ማዕከል ማስፈለጉን ጠቁመዋል።

ስለሆነም ማቆያ ማዕከሉ የቅድመ ወሊድ ክትትል ዕድልን በመፍጠር የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ሞትን ለመቀነስ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።


 

በጤና ጣቢያው የተገነባው የእናቶች ማቆያ ማዕከል መታጠቢያ ቤትን ጨምሮ ምግብ ማብሰያ፣ ማረፊያ ክፍሎችና እናቶች የሚዝናኑበት የመዝናኛ ማዕከልን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።

እናቶች በቆይታቸው ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ እንዲመገቡ እንደሚደረግ ገልፀው በዚህም አርሶ አደሩን ጭምር ያሳተፈ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መና መኩሪያ በበኩላቸው፤ በክልሉ የእናቶችና የጨቅላ ህፃናት ሞትን ለመቀነስ የተቀናጀ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።


 

እናቶችን የመንከባከብ ስራ ሀገርን የማስቀጠል ስራ እንደሆነ የገለፁት አቶ መና እናቶች ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ያሻቸዋል ብለዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መና መኩሪያ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ካሰች ኤሊያስን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራር አባላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም