ቀጥታ፡

በክልሉ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው

ሐረር፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት የህዝብን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ያረጋገጡ መሆናቸውን የክልሉ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመጠቀም ቀጣይነት ያለው ልማት ማረጋገጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

እየተካሄደ የሚገኘው የሐረሪ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ አመት 9ኛ መደበኛ ጉባኤ የአስፈፃሚውንና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት የግማሽ በጀት አመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።

የምክር ቤቱ አባላት በወቅቱ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት የህዝብን ተጠቃሚነት በተጨባጭ ያረጋገጡ ናቸው።


 

የክልሉን ሁለንተናዊ ዕድገት እና የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትም የበለጠ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተከናወኑ ተግባራት በማሕበራዊና በምጣኔ ሃብት ዘርፎች እንዲሁም በኮሪደር ልማት ውጤቶች መምጣታቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ ቅንጅታዊ አሰራርነ ማጠናከርና ዘላቂነት ያለው ልማት ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


 

የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት 3 ቢሊየን 815 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አንስተው የተገኘው ገቢ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት አንፃር በ29 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።

ነገር ግን በግማሽ በጀት አመቱ ለመሰብሰብ ከታቀደው እና የክልሉ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ሀብት አንፃር የሚፈለገውን ገቢ የመሰብሰቡ ስራ ትኩረት እንደሚጠይቅ ገልፀዋል።

በክልሉ ቀጣይነት ያለው የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጠና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጣ ለመሰብሰብ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የሐረሪ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ በክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር ኦርዲን በድሪ የቀረበውን ሪፖርት በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን በአሁን ሰአት በተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ላይ እየተወያየ ይገኛል።

ምክር ቤቱ በመደበኛ ጉባኤው ከ743 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት ያጸደቀ ሲሆን ተጨማሪ በጀቱ ለመደበኛና ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ እንደሚውልም ተመላክቷል።

ጉባዔው በተጨማሪም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ በማሳለፍ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም