ቀጥታ፡

አዲስ አበባ እንግዶቿን በአዳዲስ ውብ መስህቦችና በደማቅ መስተንግዶ እየተቀበለች ነው

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦አዲስ አበባ  ለእንግዶቿ በአዳዲስ ውብ መስህቦችና በምቹ አገልግሎትና መስተንግዶ ደማቅ አቀባበል እያደረገች መሆኗን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በ39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ ለሚመጡ እንግዶች መዲናዋ ያደረገችውን ዝግጅት በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል።

ከንቲባዋ ''አፍሪካውያን ወንድሞች የአፍሪካ ኅብረት መሰረት፣ ሦስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ማዕከልና ሁለተኛ ሀገራችሁ ወደሆነችው ኢትዮጵያና ወደ አዲስ አበባ እንኳን በሰላም መጣችሁ'' ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ሀገር ጎብኝዎችና በተለያየ ምክንያት ለሚመጡ እንግዶች ያላት ምቹ ሁኔታ እያደገ መጥቷል ብለዋል።

ወደ ኢትዮጵያ እና ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ከንቲባዋ ይህም ከተማዋ ያላትን የስህበት ማዕከልነት ያረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።  

አዲስ አበባ የምታዘጋጃቸው ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መሆናቸውን በተግባር የሚያሳይ ስለመሆኑም አክለዋል።

በመዲናዋ 39ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤና፣ የጣሊያን-አፍሪካ ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ ለማካሔድ ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የጉባኤው አካል የሆኑ የተለያዩ ስብሰባዎችም በስኬታማነት መካሔድ መጀመራቸውን ጠቁመው ለዚህም አዲስ አበባ ቀደም ብላ በልዩ ትኩረት ዝግጅት ማድረጓን ነው ያወሱት።

ከንቲባ አዳነች በማብራሪያቸው በአዲስ አበባ የሚካሔዱ የልማት ሥራዎች በጥራትና በፍጥነት እውን እየሆኑ መምጣታቸው የመዲናዋን ተወዳዳሪነትና ተፈላጊነት በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

ዘንድሮም አዳዲስ መንገዶች፣ ሆቴሎች፣ የንግድ ማዕከላት፣ መናፈሻዎችና መሰል መሰረተ ልማቶች በተሟላ ሁኔታ መገንባታቸውን ገልጸው ይህም የከተማዋን ገጽታና ተወዳዳሪነት በእጅጉ ከፍ ማድረጉን አንስተዋል።

እንዲሁም በመንግሥትና በግል አጋርነት በቂና ደረጃውን የጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።  

አዲስ አበባ በሁሉም መስክ አስፈላጊውን ዝግጅት በማሟላት በጉባኤው ለመሳተፍ ለሚመጡ እንግዶች በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ  ደማቅ አቀባበልና ምቹ መስተንግዶ እያደረገች ነው ብለዋል።

የመዲናዋ ነዋሪዎችና አገልግሎት ሰጪዎች በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት ባህል እንግዶችን በአግባቡ  እንዲቀበሉና እንዲያስተናግዱ ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም