ቀጥታ፡

በአምራች ኢንዱስትሪው እየታየ ያለው መነቃቃት መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ድጋፍና ክትትል ውጤት ነው

ደብረ ብርሃን ፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦ በአምራች ኢንዱስትሪው እየታየ ያለው መነቃቃት መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ድጋፍና ክትትል ውጤት መሆኑን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ አህመዲን መሐመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

በደብረ ብርሃን ከተማ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ አራት አምራች ኢንዱስትሪዎች ተመርቀው ወደ ምርት ገብተዋል።


 

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ አህመዲን መሐመድ(ዶ/ር) በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ መንግስት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ ኢንዱስትሪ ነው።


 

በዘርፉ ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን በመለየትና መፍትኤ በመስጠትም አሁን ላይ ተጨባጭ ውጤት መምጣቱንም ገልጸዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኢንዱስትሪው መነቃቃት ትልቅ ዕድል መፍጠሩንም አንስተዋል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ46 በመቶ ያልበለጠ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት 64 በመቶ መድረሱን አመልክተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ብቻም 93 በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ አንቀሳቃሾች ወደ መካከለኛ የአምራች ኢንዱስትሪ መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።

መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪ በሰጠው ድጋፍና ክትትል በዘርፉ መነቃቃት መፍጠሩንም ተናግረዋል።


 

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው፣ በክልሉ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ በአማራ ክልል 85 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መሸጋገራቸው ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለተኪ ምርት ዕድገት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

የደብረ-ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት፣ ከተማዋ ምቹ የኢንዱስትሪ መዳረሻ እንደመሆኗ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ቁጥር እያደገ ነው ብለዋል።


 

ለዚህ ደግሞ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ተገንብተው ወደ ሥራ የገቡ የዱቄት፣ የፕላስቲክና የጫማ ማምረቻ አራት ኢንዱስትሪዎች ማሳያ ናቸው ብለዋል።

በከተማዋ በበጀት ዓመቱ እስካሁን ድረስ 15 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ጠቁመው፣ በዚህም ከ7ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም