ቀጥታ፡

የእናቶችና ህፃናት ሞትን ለመቀነስ በተደረገው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል 

ሳውላ፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የእናቶችና ህፃናት ሞትን ለመቀነስ በተደረገው ጥረት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ የጤናማ እናትነት ወር  በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።


 

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መና መኩሪያ እለቱን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ በክልሉ በወሊድና ተያያዥ ችግሮች ሳቢያ ያጋጥም የነበረን የእናቶችና ህፃናት ሞት ለመቀነስ በተሰራው ስራ ምጣኔውን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል።

በዚህም በክልሉ የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ሞትን  80  በመቶ መቀነስ መቻሉን ጠቅሰው በ2030 እናቶችና ጨቅላ ህፃናትን የመታደግ ቅንጅታዊ ስራው ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በጤና ተቋማት ለእናቶችና ለጨቅላ ህፃናት የሚሰጠውን በቴክኖሎጂ የታገዘ የጤና አገልግሎትን ይበልጥ ለማዘመን የክልሉ ጤና ቢሮ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

በጤና ጣቢያዎች ጭምር መለስተኛ ቀዶ ጥገና ለመስጠት የሚያስችሉ የህክምና ቁሳቁሶችን በሟሟላት የጤና ተቋማትን አቅም የማሳደግ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት ።


 

የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ምናሴ ኤሊያስ በበኩላቸው፤ የእናቶችና የጨቅላ ህፃናት ጤና መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በተደረገው ርብርብ አበረታች ለውጥ መታየቱን ጠቁመዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ካሰች ኤሊያስን ጨምሮ፣ የጤና ቢሮ ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም