ለሀገር ዘላቂ ሰላም ቤተ እምነቶች ያላቸውን አስተዋጽኦ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር ዘላቂ ሰላም ቤተ እምነቶች ያላቸውን አስተዋጽኦ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል
ሆሳዕና፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦ለሀገር ዘላቂ ሰላም ቤተ እምነቶች ያላቸውን አስተዋጽኦ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለፁ፡፡
"ሐይማኖቶች ለሰላም፣ ለአንድነትና ለአብሮነት" በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሆሳዕና ከተማ ለሁለት ቀናት ያካሄደው 6ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ ዛሬ ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ የሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ርብርብ እና አስተዋጽኦ ያስፈልጋል።
በመሆኑም ሰላምን ለማጽናት በሚከናወኑ ሥራዎች ሁሉም ቤተ እምነቶች የሰላምን ትሩፋቶች ለህብረተሰቡ በማስገንዘብ ሲያደርጉት የነበረውን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በስነ ምግባር የታነጸ፣ ለሀገር ሰላምና ሁለንተናዊ እድገት የሚተጋ ዜጋ በመፍጠር ረገድ የቤተ እምነቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመንግስት በኩል ለአለመግባባት መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ለዘላቂ ሰላም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህ ስኬት የሰላም ኮንፍረንሱ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ሁሉም ቤተ እምነቶች ሰላምን ለማጠናከር በየተቋማቸው እያከናወኑት ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ ብዝሃ እምነቶችና ሀይማኖቶች ተከባብረውና ተደማምጠው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን የገለጹት ደግሞ የሰላም ሚኒስቴር ተወካይ አምባሳደር እሸቱ ደሴ ናቸው።
ሰላምን በማጽናትና የህዝቦችን አብሮነት በማጠናከር ረገድ ቤተ እምነቶች ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ ግጭቶችን በመከላከል ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በትብብር የሚሰራውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ መልከፄዴቅ በበኩላቸው፤ ሰላሟ የተረጋገጠ ሀገር ለትውልድ ማቆየት የሰላም ኮንፍረንሱ ዋነኛ ትኩረት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ልዩነትን በማክበርና እንደ ውበት በመጠቀም የጋራ አጀንዳዎች ላይ ብቻ በማተኮር ለጋራ ተጠቃሚነት መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በመድረኩ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮችና የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።