የቡና ጥራትን በማስጠበቅ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ የማሳደግ ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቡና ጥራትን በማስጠበቅ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ የማሳደግ ስራ እየተከናወነ ነው
ጊምቢ፤ የካቲት 5/2018 (ኢዜአ)፡-የቡና ጥራትን በማስጠበቅና ግብይትን በማሳለጥ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የቡና ፈስቲቫል በጊምቢ ከተማ የተካሄደ ሲሆን ባለሥልጣኑ የቡና ጣእምና ጥራት ማረጋገጫ ማዕከልንም ዛሬ በይፋ ስራ አስጀምሯል።
በፌስቲቫሉ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን መሠረታዊ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ቆርቾ እንዳሉት፤ የቡና ጥራትን በማስጠበቅና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳለጥ የቡና አምራቹን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በቡና አምራች አካባቢዎች የቡና ጥራትና የጣእም ደረጃ የሚያረጋግጡ ማዕከላት በቅርበት እየተከፈቱ መሆኑን ጠቁመው ይህም ቡና አምራቹ አርሶ አደርና በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች ለጥራት ትኩረት እንዲሰጡ ያነሳሳል ብለዋል።
የቡና ጥራትን በዘላቂነት ለማስጠበቅ መንግስት የተለያዩ ድጋፎች ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
እንዲሁም አርሶ አደሮች ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት እንዲሰበስቡም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።
ይህም የቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሀገራችን ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ እያሳደገው እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የምእራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፈ በበኩላቸው፤ በዞኑ ቡናን በብዛትና በጥራት በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ የማቅረብ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ የቡና ጣእምና ጥራት ማረጋገጫ ማዕከል ወደ ስራ መግባቱም ይህንን ስራ ለማጠናከር እና የዞኑ ቡና አምራች አርሶ አደርን የረጅም አመታት ጥያቄ የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል።
የዞኑን የቡና ምርት ጥራት ደረጃን ለማሻሻልም ቡና አምራች አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ አመራሮች እና ባለሙያዎችን ያሳተፈ ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል።