ቀጥታ፡

48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2018(ኢዜአ)፦ 48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ተጠናቋል።

ስብሰባው “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ከትናንት ጀምሮ በህብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ሲካሄድ ቆይቷል።

የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶችና የሕብረቱ ተቋማት አመራሮች ተሳትፈዋል።

ምክር ቤቱ በጥር ወር 2018 ዓ.ም 51ኛው የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ በተወያየባቸው አጀንዳዎች ላይ ምክክር አድርጓል።

የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችንም አጽድቋል።

የምክር ቤቱ ስብሰባ የአፍሪካ ሕብረት ተቋማትና አደረጃጀቶች፣ በምክር ቤቱ ስር የሚገኙ ኮሚቴዎችና ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዲሁም የአጀንዳ 2063 የአፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል።

የውሃ ደህንነት እና የንጽህና፣ አጠባበቅ፣ የአጀንዳ 2063 ትግበራንና አህጉራዊ ትስስር፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ የሰው ኃይል ልማት፣ ተቋማዊና የፋይናንስ ሪፎርሞች፣ ቀጣናዊ አጋርነትና አፍሪካ በዓለም መድረክ ያላት ሚና ጉባኤው ከመከረባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

አፍሪካ እ.አ.አ በ2025 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የነበራትን ተሳትፎም ገምግሟል።

ምክር ቤቱ በስብሰባው ምርጫዎችን በማካሄድ ለአፍሪካ ህብረት አደረጃጀቶች የሚሾሙ ሰዎችን መርጧል።

ሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት አባል ሆናም ተመርጣለች።

የአፍሪካ ህብረት ቁልፍ የሰው ሀብት ሪፎርም አካል የሆነው የክህሎት ኦዲቲና የብቃት መለኪያ ሂደት(SACA) ያለበት ደረጃ ላይም ተወያይቷል።

የህግ ማዕቀፎች እና የአስተዳደር ጉዳዮች ላይም መክሯል።

የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበርነትን አንጎላ ለብሩንዲ አስረክባለች።

የአንጎላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ተሰናባቹ የምክር ቤቱ ሊቀመንበር አምባሳደር ቴቴ አንቶኒዮ ምክር ቤቱ በተለያዩ አህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ በመምከር በስኬት መጠናቀቁን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም