ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ለቀጣናው በጋራ ማደግ ወሳኝ በመሆኑ ለስኬቱ የሁሉም ጥረት ያስፈልጋል

ሐዋሳ፤ የካቲት 5/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ለቀጣናው በጋራ ማደግ ወሳኝ በመሆኑ ለስኬቱ የሁሉን ጥረት እንደሚያስፈልግ ምሁራን አስገነዘቡ።

የኢትዮጵያ የባሕር በር መብት ከሕግ፣ ከታሪክና ከመልካዓ-ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ተቀባይነት ያለው ከመሆኑም በላይ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መረጋጋትና በጋራ ማደግ ወሳኝ መሆኑንም ነው ምሁራኑ ለኢዜአ የተናገሩት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ደመቀ አጭሶ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ የመልማትና የኅልውና ጉዳይ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።

ይህን እውን ለማድረግ እየተሄደበት ያለው ዲፕሎማሲያዊና ሕጋዊ ተግባር ፍትሐዊ ተጠቃሚነትንና ለቀጣናው አብሮ የማደግ ዓላማን ለማሳካት ጠቀሜታው የጎላ ስለመሆኑም አመላክተዋል።

የቀይ ባሕርና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የብዙ ኃይሎች ፍላጎት ያለበት በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ ጥቅሟን ለማስከበር የምታደርገው ጥረት አካል መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የቀጣናው ሀገራት በብሔራዊ ጥቅሞቻቸው፣ በባህል፣ በመልከዓ-ምድርና በሌሎችም ጉዳዮች የተሳሰሩና በጋራ የማደግ ዕድል ያላቸው በመሆኑ ሊተባበሩ እንደሚገባም መክረዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ተጠቅማ ዓለም አቀፍ ንግድና የውጭ ግንኙነቶችን ስታደርግ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ ያሉት ደግሞ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ንጉሥ በላይ (ዶ/ር) ናቸው።

ይህን የታሪክና የሕግ መሰረት የተከተለ የኢትዮጵያ የባሕር በር መብትን ማረጋገጥ የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ ለማደግ በመግባባት፣ በሰጥቶ መቀበልና በትብብር ማዕቀፍ ከመሥራት ባለፈ ሀገራቱ ሰላምን ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ ጨምሮ ትልልቅ የልማት ሥራዎች በመፈጸም የዓለም የስበት ማዕከል ወደመሆን መጥታለች፤ ይህም ለቀጣናው ሀገራት የማደግ ዕድል የፈጠረ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

በተለይም የቀጣናው ሀገራት በማኅበራዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የተሳሰሩና መነጣጠል የማይቻሉ መሆኑን አንስተው፤ ይህን ዕድል ለልማት ለማዋል በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የዲፕሎማሲና የውጭ ፖሊሲ ተመራማሪ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የባሕር በርን ለማረጋገጥ የጀመረችው የዲፕሎማሲ ጥረት በተሳካ መልኩ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

ሰላማዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ሕጋዊ መንገዱን ከግብ ለማድረስም የዜጎች የነቃ ተሳትፎን ጨምሮ የቀጣናው ሀገራት ቀና ምላሽ አስፈላጊ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም