በክልሉ የተቀናጀ የግብርና አሰራር ስርዓትን በመተግበር የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተቀናጀ የግብርና አሰራር ስርዓትን በመተግበር የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል
ወልቂጤ፤ የካቲት 5/2018 (ኢዜአ):- በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተቀናጀ የግብርና አሰራር ስርዓትን በመተግበር የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉ ተመላከተ።
በክልሉ ጉራጌ ዞን በምግብ እና በሃድያ ዞን በእንስሳት ሀብት ልማት ማጠናከሪያ ፕሮግራም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ላይ የመስክ ምልከታ ተካሄዷል፡፡
የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተሰሩ የመስኖ ልማት፣ በክላስተር የለማ የቡና ማሳና የቡና ችግኝ ጣቢያ ላይ ምልከታ የተደረገ ሲሆን በጎታም ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይም ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ አህመድ ሀቢብ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ እየተተገበሩ ያሉ የግብርና ኢኒሼቲቮች የአርሶ አደሩን ህይወት እየቀየሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር፣ ለኢንዱስትሪ በቂ ምርት ለማቅረብና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት የሚያስችል ዕድል እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ዝርያቸው የተሻሻሉ እና ምርታማ የሆኑ የቡና ችግኞችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማጎልበት እየተቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ ከበሩ በላይ በበኩላቸው በምርምር፣ በውሃ እና መስኖ፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብዓት አቅርቦት፣ በገበያ መሰረተ ልማት ግንባታና ትስስር ስኬታማ ስራዎች ተመዝግበዋል ብለዋል።
የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ በምግብ ራሱን እንዲችል ከማድረግ ባለፈ ያመረተውን ምርት ወደ ገበያ በማውጣት ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ የማድረግ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
የስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራሙ በክልሉ በአራት ዞኖች በሚገኙ አስር ወረዳዎች ከ78 በላይ በሚሆኑ ፕሮጀክቶች በስኬት እየተከናወነ መሆኑንም አንስተዋል።
በክልሉ የቸሀ ወረዳ ነዋሪው አቶ ጀማል ባድሳዊ መንግስት ጥምር ግብርና ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ ምርትና ምርታማነታቸውን በማሳደግ ህይወታቸው መቀየሩን ተናግረዋል ።
ክፍት የተደረገው የጎታም ድልድይ ለአካባቢው ማህበረሰብ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት እና የግብርና ግብዓትን በወቅቱ ለማግኘት እንደሚያስችላቸውም ተናግረዋል።
በቀረበላቸው የሶላር ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ከወንዝ ውሃ በመጥለፍ በማህበር ተደራጅተው አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን የተናገረችው ደግሞ ወይዘሪት አምሪያ ሙንታቃ ናት።
በመስክ ምልከታው መርሐ ግብር ላይ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች እና የአለም ባንክ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ተገኝተዋል።