የምርጫ ሥነ-ምግባርን ተከትለን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት እንሳተፋለን - ተፎካካሪ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ሥነ-ምግባርን ተከትለን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት እንሳተፋለን - ተፎካካሪ ፓርቲዎች
አሶሳ ፤የካቲት 5/2018 (ኢዜአ)፦ የምርጫ ሥነ-ምግባርን ተከትለው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት ለማካሄድ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እያከናወነች ትገኛለች።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በምርጫ በብቃትና በንቃት ለመወዳደር ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ይገልጻሉ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጠቅላላ ምርጫው መሳተፍ የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ቤሕነን) ሊቀመንበር አብዱሰላም ሸንገል ፓርቲያቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃ-ግብር መሠረት ዕጩዎቹን እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
የምርጫ ሥነ-ምግባርን የተከተለ ሰላማዊ፣ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ለፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ግንዛቤ በማስጨበጥ በምርጫው በንቃት መሳተፍ የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ በቴክኖሎጂ መታገዙ ዕጩዎች ባሉበት ሆነው በቀላሉ እንዲመዘገቡና ጊዜና ወጪያቸውን እንዲቀንሱ ዕድል የፈጠረ መሆኑንም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።
የምርጫው ሂደት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆነና መራጩ ህዝብም በንቃት እንዲሳተፍ ከክልሉ መንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑንም አንስተዋል።
የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲ ንቅናቄ(ጉሕዴን) ሊቀመንበር ግራኝ ጉዴታ በበኩላቸው፤ ለጠቅላላ ምርጫው ዕጩዎችን ከማስመዝገብ ጀምሮ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የሰላም ሁኔታው አስተማማኝ በመሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸውን በቀላሉ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ ለምርጫው ሰላማዊ ሂደት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
ፓርቲያቸው የፖለቲካ አለመግባባቶች በውይይት ሊፈቱ ይገባል የሚል ጽኑ እምነት እንዳለው የገለጹት ሊቀ መንበሩ፣ከሀሳብ የበላይነት ይልቅ ነፍጥ የመረጡ አካላት ወደ ሰላማዊ ውይይት መምጣታቸው ለምርጫው ምቹ መደላድል ፈጥሯል ብለዋል።
በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ክልሉ በነበረበት የጸጥታ ችግር ምክንያት ፓርቲያቸው ተወዳዳሪ መሆን አለመቻሉን አስታውሰው፤ አሁን ባለው ሰላማዊ ከባቢ በምርጫው በንቃት ለመወዳደር ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።