ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን በማሳየት ያለፈው ብቻ ሳይሆን የመጻዒው ፓን አፍሪካኒዝም አርዓያነቷን አጠናክራ ቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በየዓመቱ በሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን በማሳየት ያለፈው ብቻ ሳይሆን የመጻዒው ፓን አፍሪካኒዝም አርዓያነቷን አጠናክራ ቀጥላለች ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ በአዲስ አበባ የሚካሄደውን 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና የአፍሪካ ጣልያን ጉባኤን አስመልክቶ  መግለጫ ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ በሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን በማሳየት ያለፈው ብቻ ሳይሆን የመጻዒው ፓን አፍሪካኒዝም አርዓያነቷን አጠናክራ ቀጥላለች ብሏል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ኢትዮጵያ የአህጉራዊ አንድነትና የፓን-አፍሪካኒዝም ማሳያ የሆነውን 39ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤን እንዲሁም ጎን ለጎን የሚካሄደውን የታሪካዊውን የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባኤን በድምቀት ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች።

ከየካቲት 6 እስከ 8 ባሉት ቀናት ሃገራችን ሁለት ዐበይት ጉባዔዎችን ታስተናግዳለች።

የመጀመሪያው የካቲት 6 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደው የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባኤ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለ39ኛ ጊዜ የሚካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ነው።

የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ፣ “የ2063 የአጀንዳ ግቦችን ለማሳካት ዘላቂ የውሃ አቅርቦት እና ደህንነቱ የተጠበቀ የንፅህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል።ይህ ርዕሰ ጉዳይ የአፍሪካን ለዘላቂ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ የ2063 አጀንዳን ከግብ ለማድረስ የረጅም ጊዜ ራዕይን በመሰነቅ እየገሰገሰች መሆኗን የሚያመላክት ነው።

ከዚህ አንጻር ሃገራችን ለአፍሪካውያን ልታቀርባቸው የምትችላቸው በርካታ ተሞክሮዎች አላት። ሃገራችን ኢትዮጵያ፦

• በአረንጓዴ አሻራ ባለፉት ሰባት ዓመታት ወደ ሃምሳ ቢሊዮን የሚገመት ችግኝ በመትከል የደን ሽፋናችንን ከ17 በመቶ ወደ 23 በመቶ ማሳደግና ለአዛላቂ ልማት ያለንን ቁርጠኝነት ማሳየት ችለናል።

• ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የሃይድሮ፣ የነፋስ እና የጸሃይ ታዳሽ ሃይል አማራጮችን በመጠቀም የኢነርጂ ፍላጎቷን ከማሳደግም አልፎ ለጎረቤቶች ጭምር መትረፍ ችላለች። በተጨማሪም በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በመከልከል ለታዳሽ ኢነርጂ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይታለች።

• በከተማ የኮሪደር ልማት እና በወንዝ ዳርቻ ልማት ከተሞችን ጽዱና ውብ ማድረግ እና የአካባቢ ብክለትን የቀነሱ ደማቅ ከተሞችን የመፍጠር ጥረት በመዲናችን ጀምራ በበርካታ የሃገራችን ከተሞች እየቀጠለች ትገኛለች።

• ከፕላስቲክ የጸዳ አካባቢን ለመፍጠር የአንድ ጊዜ የፕላስቲክ መያዣዎችን በመከልከል ለዘላቂ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም አስመስክራለች።

• በቀጣይነትም የውሃ ሃብቷን በአግባቡና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችሉ ሁለንተናዊ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች።

ከኅብረቱ ጉባኤ አስቀድሞ የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባኤ የሚካሄድ ሲሆን፣ ይህም የአፍሪካ-ኢጣሊያ የትብብር ማዕቀፎችን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው። የአፍሪካ ጣሊያን ፎረም መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከሮም ውጭ ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያው ሲሆን በአፍሪካ አፈር ሲካሄድ የመጀመሪያዋ መዳረሻ ኢትዮጵያ መሆኗ ሃገራችን አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ከማስተሳሰር አንጻር ያላትን ከፍተኛ አቅም የሚያሳይ ነው።

የጉባዔው ማዕከላዊ አጀንዳ እ.ኤ.አ በ2024 በሮም ይፋ የተደረገውን የማቴይ ዕቅድ አፈጻጸም መገምገም እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ነው።

የጉባኤው ዋና ዋና አምዶች በሆኑት ኢነርጂ፣ ግብርና፣ ትምህርትና ስልጠና፣ ጤና፣ ውሃ፣ መሰረተልማት ሃገራችን በርካታ ተሞክሮዎችን ማቅረብና አጋርነቶችን መመስረት የሚያስችላት ቁመና ላይ ትገኛለች።

በእነዚህ ጉባኤዎች ርዕሰ ብሔሮች፣ ጠቅላይ ሚንስትሮች፣ ምክትሎች እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ17 ሺህ በላይ የልዑካን ቡድን አባላት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እነዚህን ጉባዔዎች ለመዘገብ ከ800 በላይ የሚዲያ ባለሞያዎች ፈቃድ ጠይቀዋል። በቀጣይ ቀናት የአህጉራችን ዋና ዋና ሚዲያዎች ዐይን እና ጆሮ ሃገራችን ላይ ያነጣጥራል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስጠብቁ እና ከግብ በሚያደርሱ ውይይቶች ላይ በንቃት ለመሳተፍ ተዘጋጅታለች። በዚህም የአፍሪካ የጋራ ጥቀሞችን ለማረጋገጥ የበኩሏን አስተዋጽኦ ታደርጋለች። የአፍሪካ መሪዎችና ልዑካን ቡድኖች በቆይታቸው ከዲፕሎማሲያዊ ስራዎቻቸው ባሻገር፣ የሀገራችንን የልማት ሥራዎች እና የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲጎበኙና በቀጣይነት እየተመዘገቡ ያሉ የልማት ውጤቶቻችንን እንዲመለከቱ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል።

እንደ አስተናጋጅ ሀገር፣ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ መሪዎች ልዑክ እና እንግዶችን ተቀብላ ለማስተናገድና በርካታ ሁለትዮሽ ውይይቶችን ለማድረግ ዝግጁ ናት።

የኅብረቱ መቀመጫ እና የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ከአህጉሩ እና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ መሪዎችን እና የልዑካን ቡድኖችን ተቀብላ ለማስተናገድ ከምንጊዜውም በላይ የተሟላ ዝግጅት አድርጋለች።

በአጠቃላይ እንደ መንግስት እነዚህን ሁለት ጉባኤዎች ስኬታማ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ የሚከተሉት ዋና ዋና ተግባራት ተከናውነዋል፦

👉 የተቀናጀ አመራር ከመስጠት አንጻር፦ 35 የፌዴራል ተቋማትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያሉበት ዐቢይ ኮሚቴ ስራዎቹን በውጤታማነት ሲመራ ቆይቷል።

👉የዲፕሎማሲና መስተንግዶ ዝግጅት፦ ከ180 በላይ በሁሉም የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋዎች ብቁ የሆኑ የበጎ ፈቃድ ካዴቶች መሰረታዊ ሥልጠና ወስደው ተሰማርተዋል።

👉 የመግቢያ ፈቃዶችን ከማሳለጥ አንጻር፦ የቪዛ፣ የጉምሩክና የሚዲያ ፈቃድ አገልግሎቶች በተሳለጠ ሁኔታ እንዲሰጡ ልዩ አሰራር ተዘርግቶ ሥራ ላይ ውሏል። በዚህም ሁሉም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ያሉበት ፖርታል ተዘጋጅቶ የሰው ንክኪ በቀነሰ መልኩ በኦንላይን ተከናውነዋል።

👉 አገልግሎትን በተመለከተ፦ ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አቅራቢዎችና የታክሲ አሽከርካሪዎች እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ለመቀበል ስልጠና ወስደዋል። እንደ መብራትና ቴሌኮሚኒኬሽን ያሉ መሠረተ-ልማቶችም በላቀ ዝግጁነት ላይ ይገኛሉ።

👉ሰላምና ደህንነት አንጻር፦ የጸጥታና ደህንነት ግብረ-ኃይሉ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ታግዞ ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተማማኝ ዝግጅት አድርጓል።

ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም ማዕከልነትና ዲፕሎማሲያዊ ሚና በኩል አህጉሩ የአንድነት ድምጽ እንዲኖረው በማድረግ፣ በሰላም ማስከበር ስምሪቶች ላይ ቀዳሚ ተሳትፎ በማድረግ፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና (AFCFTA) ስምምነትን በፍጥነት በማጽደቅ፣ ለተለያዩ የአህጉሪቱ ተቋማት አስፈላጊውን የመሰረተ ልማት በቅረብ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያላት ሀገር ነች።

ውድ የሀገራችን ሕዝቦች

ይህን ጉባኤ ማዘጋጀት ለእኛ የዲፕሎማሲያዊ ስኬት ማሳያ ብቻ አይደለም ይልቅም አፍሪካውያን ወንድሞቻችን እንደ ሃገር በተፈተንባቸው ወቅቶች ሁሉ ላሳዩን አብሮነት እና ወዳጅነት ምስጋናችንን የምንገልጽበትና አፍሪካዊ አንድነታችንን የምናጸናበት ቋሚ መድረካችን ነው።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ እያደረገች ባለቸው ሰፊ የሪፎርም ስራ፣ በምግብ ሉአላዊነት፣ በኮሪደር ልማት እና በአረንጓዴ አሻራ ትግበራ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም በምሳሌነት የምትጠቀስ ሃገር ሆናለች። እንደ ስሟ አዲስ እና ውብ እየሆነች የመጣችው አዲስ አበባ በአዳዲስ የከተማ መሰረተ-ልማቶቿ እና እንግዳ ተቀባይ ህዝቧ አህጉር አቀፍና አለም አቀፍ ሁነቶችን የማዘጋጀት ብቃቷ ጎልብቶና ፈክቶ በእጅጉ እያሸበረቀ ይገኛል።

ክቡራን የመዲናችን አዲስ አበባ እና ዙሪያ የሚገኙ ከተሞች ነዋሪዎች

ይህ ታላቅ አህጉራዊ ኩነት በስኬት እንዲጠናቀቅ የሁሉም ዜጎች የተቀናጀ ትብብር ወሳኝ በመሆኑ እስከ ጉባኤው ፍጻሜ ድረስ በሚኖሩት ጥቂት ቀናት፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ መጠነኛ መስተጓጎሎችን ሀገራችን ከምታገኘው ዘርፈ-ብዙ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ጥቅም ግንዛቤ ዉስጥ በማስገባት የበኩላቸዉን ደርሻ እንዲወጡ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።

በመጨረሻም ይህ ቅድመ-ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሌት ተቀን ለሰሩ የፌዴራልና የከተማ አስተዳደር ተቋማት፣ ማህበራት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች ሁሉ በመንግስት ስም የላቀ ምስጋና እናቀርባለን።

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት

የካቲት 5 ቀን 2018

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም