ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ያላትን አርአያነት በተግባር እያሳየች ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ያላትን አርአያነት በተግባር እያሳየች ትገኛለች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤና አዳዲስ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በማካሄድ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አርዓያነቷን በተግባር እያሳየች መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤና የአፍሪካ ጣሊያን ስብሰባ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በመግለጫቸው፤ ኢትዮጵያ በቀጣይ ሶስት ቀናት የአፍሪካ ጣሊያን እና የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤን ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች ብለዋል።
የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መሪ ሀሳብ አፍሪካ የሕብረቱን የ2063 አጀንዳ የልማት ግቦችን በማሳካት ለዘላቂ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በውሀ ሀብት ልማትና ጥበቃ ለአፍሪካ ሀገሮች ትምህርት የሚሰጥ ልምድና ተሞክሮ እንዳላት በመግለጽ፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋኗን ከ17 በመቶ ወደ 23 በመቶ ማሳደግ ችላለች ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በማጠናቀቅ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የሀይል አቅርቦት ተደራሽነት ማስፋት የሚያስችል ትስስር መፈጠሩን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች በክልል ከተሞች ጭምር በማስፋት የውሀ ሀብትን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ሁለንተናዊ ርምጃ እየወሰደች መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተሟላ ዝግጅት ማድረጓን በመጥቀስ፤ የተቀናጀ አመራር፣ የተሳለጠ የትራንስፖርት፣ በአፍሪካ ሕብረት የስራ ቋንቋዎች የበቁ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭ ካዴቶች፣ የመብራትና የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ጎባኤው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት በማሳያ ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ቋሚ ወዳጅነታችንን የምናጸናበት ነው ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤና ዓለም አቀፍ ሁነቶች አዳዲስ ሁነቶችን በማሳየት ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አርዓያነቷን በተግባር እያሳየች መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር በመዲናችን አዲስ አበባ ነገ የሚካሄደው የአፍሪካ ጣሊያን ስብሰባ በአፍሪካ ምድር ሲካሄድ የመጀመሪያው መሆኑን ተናግረዋል።
ስብሰባው በውሃ፣ ግብርና፣ ኢነርጂ፣ ትምህርትና ስልጠናና ጤና ዘርፎች ያተኮረ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ተሞክሮዋን ታቀርብበታለች ብለዋል።
በዚህ ስብሰባ 17 ሺህ በላይ የልዑካን ቡድን አባላት እንደሚሳተፉ ጠቅሰው፤ የበርካታ ሀገራት የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የዘገባ ፈቃድ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
በሁነቶቹ ባሻገር የሁለትዮሽ ውይይቶች እንደሚኖሩ ገልጸው፤ የአፍሪካ ሕብረት መሪዎች የሀገራችንን ልማትና የቱሪስት ስፍራዎች ይጎበኛሉ ብለዋል።