ቀጥታ፡

ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማሻገር በመደማመጥ ሰላምን ማጽናት ቀዳሚ አማራጭ ሊሆን ይገባል

ሆሳዕና ፤የካቲት 5/2018 (ኢዜአ)፦ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማሻገር በመደማመጥ ሰላምን ማጽናት ቀዳሚ አማራጭ ሊሆን ይገባል ሲሉ በሆሳዕና ሃገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊ የኃይማኖት አባቶች ገለፁ፡፡

የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ 6ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስን በማስመልከት የተዘጋጀው የፓናል ውይይት መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ የኃይማኖት አባቶች በወቅቱ እንደገለጹት፥ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማሻገር በመደማመጥ ሰላምን ማጽናት ቀዳሚ አማራጭ ሊሆን ይገባል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መልከፄዴቅ እንዳሉት፥ የሰው ልጅ ተከባብሮና ተደማምጦ በአብሮነት መኖር እንዳለበት የሁሉም ሀይማኖቶች አስተምህሮ ያስረዳል፡፡

ወንድሞች በአብሮነት ቢኖሩ መልካም ስለመሆኑ የመፅሐፍ ቅዱስ ቃል እንደሚያስተምርም አክለዋል፡፡

''እኛ የሀይማኖት አባቶች ከልዩነት ይልቅ ተቀራርቦ በአብሮነትና በሰላም መኖርን መሰረት በማድረግ በተከታዮቻችን ዘንድ በጎ ዘርን በመዝራት ለትውልድ የተሻለች ሀገርን ማኖር ይጠበቅብናል'' ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አብድልከሪም ሼህ በድረዲን በበኩላቸው፥ የሰላም እጦት የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሀገራዊ ሰላምን በዘላቂነት አስጠብቆ ለማስቀጠል የሀይማኖት ተቋማት ተከታዮቻቸውን በማረቅ ረገድ ትልቁን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ጠቅሰው፥ በዚህም ዜጎች ተከባብረውና ተደማምጠው እንዲኖሩ ለማድረግ እንደሚያስችልም አመልክተዋል፡፡

ለትውልዱ የተሻለች ሀገርን ለማቆየት በመደማመጥ ተመስርቶ መጓዝን ቀዳሚ አማራጭ ማድረግ ይገባል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ህብረት ካውንስል ፕሬዚዳንት ቄስ ደረጀ ጀምበሩ ናቸው፡፡

በሀገር ሰላም እጦት ምክንያት ለሀገር የሚመጣ ትርፍ አለመኖሩን ባለፉት ጊዜያት በነበሩ አለመግባባቶች ትምህርት ወስደናል ነው ያሉት፡፡

የጋራ ቤታችን የሆነችው ኢትዮጵያን በጋራ በመገንባት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማድረስ የጥላቻና የልዩነት አስተሳሰቦችን የማረም ግዴታችንን ልንወጣ ይገባልም ብለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይም የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፤ የሀይማኖት አባቶችና ሌሎች እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም