ኢትዮጵያ በውኃ ዘላቂነትና ተደራሽነት ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በውኃ ዘላቂነትና ተደራሽነት ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 5/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በውኃ ዘላቂነትና ተደራሽነት ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች መሆኗን የአፍሪካ ኅብረት የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ምክር ቤት ሴክሬታሪያት ገለጸ።
የአፍሪካ ኅብረት የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ምክር ቤት ሴክሬተሪያት ኃላፊ ዊሊያም ካሪው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እያሳየ ያለው የአመራር ሚና ለአፍሪካ ኅብረት እጅግ መሰረታዊ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኅብረቱ አባል ሀገራት በማንኛውም አባላት ዘንድ የተዘረጉ መልካም ተሞክሮዎችንና ፖሊሲዎችን በአርዓያነት መጠቀም እንዳለባቸውም ለኢዜአ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት ለዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ተደራሽነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችንና አሠራሮችን መዘርጋቱን ገልጸው፤ ይህም ለሌሎች የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት መልካም ተሞክሮ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተወሰዱ የፖሊሲ ለውጦችና ቆራጥ የአመራር ሰጭነት ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ያስመዘገበችውን ስኬትም አድንቀዋል።
ይህ ትልቅ ቁጥር መሆኑን ጠቁመው፤ የአመራርና ትክክለኛ ፖሊሲዎች ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።