ቀጥታ፡

የተፋስስ ልማት ሥራ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርታማነትን በማሳደጉ አጠናክረን ቀጥለናል

ወልቂጤ፤ የካቲት 5/2018 (ኢዜአ)፡-የተፋሰስ ልማት ሥራ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርታማነትን እያሳደገ በመሆኑ ዘንድሮም አጠናክረው መቀጠላቸውን የጉራጌ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የአፈር ለምነትን በመጠበቅና የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ በማድረግ ምርታማነትን እያሳደገ በመሆኑ ዘንድሮም ልማቱን ማጠናከራቸውን ገልጸዋል።

በጉራጌ ዞን የእኖር ኤነር መገር ወረዳ አርሶአደር በደዊ ታቅንዳ በተፋሰስ ልማት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መጀመሩ በጎርፍ ተጠርጎ ይወሰድ የነበረ ለም አፈር ጥቅም ላይ ለማዋል አስችሏል ብለዋል።


 

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች የተራቆቱ መሬቶች ማገገማቸው እና የደረቁ ምንጮች ዳግም መፍለቃቸው የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በዘንድሮ የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት ሥራ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ጠረጴዛማ የእርከን ልማት ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የእዣ ወረዳ አርሶ አደር ወይዘሮ ሙርጋት ታቅንዳ በበኩላቸው ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የተከናወነው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ መሬታቸውን ከመሸርሸር መታደጉን ገልጸዋል።


 

የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የመሬት ለምነትን በመመለስ ምርታማነትን እያሳደገ በመሆኑ በዘመቻው በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተጎዱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማድረጉን የተናገሩት ሌላኛው የእኖር ወረዳ አርሶ አደር መህዲ ደሊል ናቸው።

የተፋሰስ ልማት ሥራው እየተመናመኑ የነበሩ የደንና የውኃ ሀብቶች እንዲመለሱ ማስቻሉንም ገልፀዋል ።


 

የለሙ አካባቢዎችን ከሰውና ከእንስሳት ንኪኪ በመጠበቅ ለመኖ ልማትና ለንብ ማነብ ሥራ በማዋል ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እያስቻሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በበኩላቸው እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራዎች ውጤት ተመዝግበዋል።

በተለይም ተዳፋታማ በሆኑ አካባቢዎች ጠረጴዛማ እርከን በመስራት ከምርት ውጭ የነበሩ መሬቶች አገግመው በተለያዩ ሰብሎች እንዲለማ ከመደረጉ ባለፈ ለንብ ማነብ ሥራ እየዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የደረቁ ምንጮችና በጎርፍ በመሸርሸር የተጎዱ መሬቶች ማገገማቸው የግብርና ምርትና ምርታማነትን እያሳደገው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተመዘገቡ ተጨባጭ ውጤቶች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረጋቸው በዘንድሮ ተፋሰስ ልማት የወጣቶችና የሴቶች ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ገልጸዋል።

በዘንድሮ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ በዞኑ በ23 ሺህ ተፋሰሶች ላይ 88 ሺህ 581 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም