ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ወስደዋል-ቢሮው

ወላይታ ሶዶ፤ የካቲት 5/2018 (ኢዜአ):-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መውሰዳቸውን የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ቦጋለ ቦሼ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ዜጎች በነጻነት ለመንቀሳቀስ የሚያስችላቸው ነው።

መታወቂያው የዜጎችን ትክክለኛ ማንነት ለመለየትና የወንጀል ድርጊቶችን በመከላከል ለማህበረሰቡ ሁለንተናዊ ዋስትና መረጋገጥ ጠቀሜታ እንዳለውም አንስተዋል።

በክልሉም ነዋሪዎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

እስካሁንም መታወቂያውን ለማግኘት ከተመዘገቡት 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚሆኑት ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡ 

በክልሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተሰራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መታወቂያውን ለመውሰድ የተመዘገቡ ነዋሪዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ገልጸው፣ "በበጀት ዓመቱ ለ6 ሚሊዮን ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

የፋይዳ መታወቂያ አይነስውራን አገልግሎት ለማግኘት ይደርስብን የነበረውን እንግልት በመቀየር ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ያለው ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ ተማሪ መሸሻ ማንዳዶ ነው።

መታወቂያው በተለይ እንደእሱ አይነስውራን ለሆኑ ዜጎች ተደራሽ በመደረጉ እንግልቶችን ከማስቀረት ባለፈ በነፃነት ለመንቀሳቀስ አስችሎናል ነው ያለው። 

አቶ መሳይ ሳሙኤል የተባሉ ሌላው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው "የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በንግድ ሥራችን ላይ ሊደረስ የሚችል መጭበርበርን እየታደገ ነው" ብለዋል።

መታወቂያው የዜጎችን ትክክለኛ መረጃ በተሻለ መንገድ እንዲያዝ በማድረጉ ወንጀልና ወንጀለኞችን በቀላሉ ለመከላከል የጎላ አስተዋጾ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ቴዎድሮስ ዘካሪያስ በበኩላቸው፤ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መውሰዳቸው በንግድም ሆነ በሌሎች ተግባራት ደሕንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደረዳቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም