በቦንጋ ከተማ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመት እያስቻሉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቦንጋ ከተማ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመት እያስቻሉ ነው
ቦንጋ፣ የካቲት 5/2018 (ኢዜአ)፦ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመት እንዳስቻሏቸው የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
የካፋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት በበኩሉ ገበያውን ከማረጋጋት ባለፈ ህገወጥ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል፡፡
መንግስት ገበያን ለማረጋጋት እያከናወናቸው ካሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል በየአካባቢው የተቋቋሙ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በእነዚህ ገበያዎችም በህብረተሰቡ ላይ ሲደርስ የነበረውን የኑሮ ጫና መቀነስ የተቻለ ሲሆን የግብርና ምርቶችም በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲቀርቡ ዕድል ፈጥሯል፡፡
በካፋ ዞንም ቦንጋ ከተማን ጨምሮ በዘጠኝ የዞኑ ከተሞች የሰንበት ገበያን በማቋቋም ህብረተሰቡ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እየተሰራ ነው፡፡
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ ወይኒቱ ወዳጆ በከተማው የተቋቋመው የቅዳሜና እሁድ ገበያ የአትክልትና ሌሎች የግብርና ምርቶችን በቅናሽ ዋጋ ለመሸመት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
መንግስት ገበያን ለማረጋጋት እየወሰዳቸው ያሉ የመፍትሔ እርምጃዎች የህብረተሰቡን ጫና እያቃለለ በመሆኑ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አስራት አኢሮ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች መስፋፋታቸው በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ትልቅ እፎይታ ፈጥረዋል።
ገበያዎቹ የፈለጉትን ምርት በጥራትና በብዛት በአንድ ቦታ ለማግኘት እንዳስቻሏቸው የገለፀችው ደግሞ ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ስምረት ቆጭቶ ናት።
የገበያ አማራጩ የዋጋ ጭማሪን በማስቀረት የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር ማስቻሉን ጠቅሳ፣ በቀጣይ ከግብርና ምርቶች ባሻገር የፋብሪካ ምርቶችም በተመሳሳይ ለህብረተሰቡ እንዲቀርቡ ጠይቃለች።
የካፋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ ሃብታሙ ገብረስላሴ በበኩላቸው በአምራችና ሸማች መካከል ያለውን ሰንሰለት በማሳጠር ገበያን ለማረጋጋትና ህገወጥ ንግድን ለመከላከል በቅንጅት የተሰራው ሥራ ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል፡፡
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን በማቋቋም በማህበራት አማካኝነት የተለያዩ የግብርና ምርቶች ለሸማቹ ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል ተችሏል ብለዋል።
ገበያዎቹ የዋጋ ንረትን በመከላከል የህብረተሰቡን ጫና እየቀነሱ በመሆኑ ቀጣይነታቸውን ለማረጋገጥና ለማዘመን የዞኑ አስተዳደር በ18 ሚሊዮን ብር በቦንጋ ከተማ ሼድ እያስገነባ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የገበያ አማራጮችን ከማስፋፋት ባለፈ የመንግስት ሠራተኞች ሸማች ማህበራትን በማደራጀትና 3 ሚሊዮን ብር ብድር በማመቻቸት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ባለፉት ስድስት ወራትም ከዘጠኝ ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ ክትትል በማድረግ ያለአግባብ ዋጋ በጨመሩና ህገ ወጥ ድርጊት በፈጸሙ 1ሺህ 865 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።