ቀጥታ፡

ሊቨርፑል ሰንደርላንድን አሸነፈ

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 4/2018 (ኢዜአ)፡- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት ጨዋታ ሊቨርፑል ሰንደርላንድን 1 ለ 0 አሸንፏል።

ማምሻውን በስታዲየም ኦፍ ላይት በተካሄደው ጨዋታ አምበሉ ቨርጅል ቫን ዳይክ በ61ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ያስቆጠራት ግብ ቀያዮቹን አሸናፊ አድርጋለች።

በጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ ሰንደርላንድ፣ ሊቨርፑል በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ ወስደው ተጫውተዋል።

ጃፓናዊው የሊቨርፑል የተከላካይ አማካይ ዋታሩ ኤንዶ ባጋጠመው ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት በ69ኛው ደቂቃ በጆ ጎሜዝ ተቀይሮ ወጥቷል።

የሊቨርፑል የተከላካይ ክፍል ጉዳት ቀውስ ተባብሶ ቀጥሏል።

በሊጉ 12ኛ ድሉን ያስመዘገበው የወቅቱ የዋንጫ ባለቤት ሊቨርፑል በ42 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ስምንተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ሰንደርላንድ በ36 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በዘንድሮው የውድድር ዓመት በሊጉ በሜዳው ሽንፈት ሳያስተናግድ የቆየው ብቸኛው ክለብ ሰንደርላንድ ለመጀመሪያ ጊዜ በስታዲየም ኦፍ ላይት ተሸንፏል።

በሌላኛው ጨዋታ በርንሌይ ክሪስታል ፓላስን 3 ለ 2 አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም