ቀጥታ፡

በሆሳዕና ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የልማት ስራ የከተማዋን እድገት የሚያፋጥን ነው -የሰላም ኮንፍረንስ ተሳታፊዎች

ሆሳዕና ፤ የካቲት4/2018(ኢዜአ) ፡-በሆሳዕና ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የልማት ስራ የከተማዋን እድገት የሚያፋጥን መሆኑን የሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ያዘጋጀው 6ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ "ሃይማኖት ለሰላም፣ ለአንድነትና ለአብሮነት" በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የጉባዔው ተሳታፊዎች ማምሻውን በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ የሚገኘውን ሁለንተናዊ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተሳታፊዎች በከተማው እየተከናወነ የሚገኘው የልማት ስራ ከተማዋን ውብና ለኑሮ ምቹ ከማድረግ ባሻገር የከተማዋን እድገት የሚያፋጥን መሆኑን ማየታቸውን ገልጸዋል፡፡ 


 

ከተሳታፊዎቹ መካከል የከምባታ፣ ሀላባ፣ ጠምባሮና ኮንታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁእ  አቡነ ጢሞቲዎስ  እንደገለፁት በሆሳዕና ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የልማት ስራ የከተማዋን ፈጣን እድገት የሚያረጋግጥ ነው፡፡

በከተማው አገልግሎት መስጠት የጀመረውን ክልላዊ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እንደ አብነት ያነሱት ብፁእ አቡነ ጢሞቲዎስ፤ ይኸም የተገልጋዩን እንግልት የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ዋና ፀሐፊ  ሼኽ አብድልሀሚድ አህመድ በበኩላቸው የሆሳዕና ከተማ በፈጣን እድገት ላይ እንደምትገኝ አይተናል ብለዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ፅህፈት ቤትና የአቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም ግንባታም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን መመልከታቸውን አክለዋል፡፡

የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነትን በማስፋት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝና ሌሎች አካባቢዎችም ጭምሮ ተሞክሮ የሚወስድበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 

ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካቶሊክ ቤተ እምነት የመጡት አባ ጴጥሮስ አበበ በበኩላቸው በከተማው የሀድያ የዘመን መለወጫ የሆነው "ያሆዴ" በዓል የሚከበርበት "ሀድይ ነፈራ" ማራኪ በሆነ ድባብ መልማቱን አድንቀዋል፡፡

በከተማው የተሰራው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ውበት ከመጨመሩም ባለፈ ለኑሮ፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ የሚያደርጋት መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በሆሳዕና ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙት የልማት ስራዎች የከተማዋን ውበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያፈኩ እንደሚገኙ  የተናገሩት ደግሞ በምስራቅ ጉራጌ ዞን የባህል ሽማግሌው ቀኝአዝማች ፀጋዬ ታቦር ናቸው፡፡

በጉብኝቱ ላይ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የከተማው አመራሮች፣ የሰላም ሚኒስቴር ተወካይ እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም