ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በወሳኝ የምርጫ ወቅት ላይ ናት - ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፤የካቲት 4/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በወሳኝ የምርጫ ወቅት ላይ በመሆኗ ለስኬታማነቱ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገለጹ። 

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 42 ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተናጠል፣ 15 ፓርቲዎች ደግሞ በሁለት ጥምረትና በአንድ ግንባር ለመፎካከር መመዝገባቸውንም አስታውቀዋል።

ከአጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ17 ሺህ ያህሉ የዲጂታል የመራጮች ምዝገባን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅና የጊዜ ሰሌዳ በማውጣት ወደ ትግበራ ምዕራፍ ተገብቷል።

ለዚህም ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር  በምርጫው አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ተፈናቃዮች፣ የጸጥታ ኃይል አባላትን ጨምሮ አካታችነቱን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ወሳኝ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ መሆኗን ጠቅሰዋል።

ቦርዱ ለምርጫው ውጤታማነት የምርጫ ሕጉን ከማሻሻል ጀምሮ አዳዲስ በቴክኖሎጂ የታገዙ የአሠራር ስርዓቶችን ወደ ሥራ ማስገባቱን አስረድተው፥ ይህም ግልጽና ተዓማኒ ምርጫ ለማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች በምርጫ ካርዳቸው በሀገራዊ የፖለቲካ፣ የዴሞክራሲና በህዝብ ይሁንታ የተመረጠ ጠንካራ መንግሥት በመመስረት ሂደት ትልቅ አሻራ የሚያሳርፉበት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለምርጫው ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

ቦርዱ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የዕጩዎች ምዝገባን ከጥር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በዲጂታል ስርዓት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በዚህም 42 ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተናጠል፣ 15 ፓርቲዎች ደግሞ በሁለት ጥምረትና በአንድ ግንባር ለመፎካከር ዕጩዎቻቸውን እያስመዘገቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የመራጮችን ምዝገባ በወረቀትና በዲጂታል አማራጮች በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከአጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎች መካከልም በ17 ሺህ ያህሉ የዲጂታል ምርጫ ምዝገባን ተደራሽ ለማድረግ የኢንተርኔት አገልግሎት መኖሩን በማረጋገጥ የምዝገባ መሳሪያና የዲጅታል መተግበሪያን የመዘርጋት ሥራዎች እየተሳለጡ መሆኑን አንስተዋል።

መተግበሪያው ማየት የተሳናቸው በድምጽ፣ አካል ጉዳተኞችና በተለያየ ምክንያት በምርጫ ጣቢያ በአካል መገኘት የማይችሉ ሁሉ ባሉበት ቦታ በእጅ ስልካቸው የሚመዘገቡበትን አማራጭ ያመቻቸ ነው ብለዋል።

ለምርጫው ውጤታማነት የታዛቢዎች እና የመራጮች ሚና ወሳኝ በመሆኑ የምርጫ ትምህርትና ግንዛቤን ለማስፋት ለሚሰሩ 169 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ  መሰጠቱንም  አብራርተዋል።

የምርጫ ሂደትን ነፃ፣ ገለልተኝነትና ፍትሐዊነት ለማረጋገጥም 547 አስተባባሪዎችና 129 ሺህ የእግር በእግር ታዛቢዎች ያሏቸው 45 የሀገር ውስጥ ድርጅቶች በኦንላይን ሥርዓት በታዛቢነት መመዝገባቸውን አንስተዋል።

ለዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት መጥተው ፈቃድ የሚወስዱበትን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ዜጎች በምርጫ ሂደቱ ላይ የሚሰጡት ድምጽ ዋጋ እንዳለው መገንዘብ አለባቸው ያሉት ሰብሳቢዋ፤ በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎችን የፖሊሲ አማራጮች በማጤን ይበጀኛል  የሚሉትን ሊመርጡ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ለማድረግ በሁሉም መንገድ ተዘጋጅቷል ያሉት ሰብሳቢዋ፤ ባለድርሻ አካላትም ገንቢ ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በምርጫ ሂደት ሊፈጠሩ የሚችሉ ቅሬታዎችን ምላሽ ለመስጠትም የቅሬታ አቀራረብና አፈታት የአሰራር ማሻሻያ በማድረግ በተዋረድ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ በፍጥነት የሚታይበት ሁኔታ መመቻቸቱን አንስተዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መገናኛ ብዙኃን የሚሰጧቸውን የአየር ሰዓት በመጠቀም የፖሊሲ  አማራጮቻቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ የምርጫ ሂደት ንቁ ተሳትፏቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም