ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ከ81 ሚሊየን ዩሮ በላይ የኢኮኖሚ ስምምነቶችን ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ከ81 ሚሊየን ዩሮ በላይ የኢኮኖሚ ስምምነቶችን ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የ81 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ የኢኮኖሚ ድጋፍ እና ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር የእዳ ሽግሽግ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እና የአውሮፓና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚኒስትር ልዑክ ኤሌኖር ካሮይት ተፈራርመዋል።
የድጋፍ ስምምነቱ የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ስትራቴጂካዊ የልማት አጋርነትን የሚያጠናክር እና የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ የሚደግፍ ወሳኝ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።
በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማገገሚያ ትልቅ ምዕራፍ በሆነው የእዳ ሽግሽግ ስምምነት ላይ ሁለቱ ሀገራት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ ስር እእአ ሐምሌ 2025 የመጀመሪያውን የሁለትዮሽ መግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ተገልጿል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፥ ፈረንሳይ እንደ አበዳሪ ሀገራት ኮሚቴ ሰብሳቢነቷ የመግባቢያ ስምምነቱ ስኬታማ እንዲሆን ወሳኝ ሚና መጫወቷን ገልጸዋል።
ከዕዳ እፎይታው በተጨማሪ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ (HGER 2.0) የ80 ሚሊየን ዩሮ የበጀት ድጋፍ እና 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ የቴክኒክ ድጋፍን ያካተተ አዲስ የፋይናንስ ማዕቀፍ ከፈረንሳይ ጋር ተፈርሟል።
ይህም ፈረንሳይ በመጀመሪያው የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ወቅት ያደረገችው የ100 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አካል ነው።
የአውሮፓ እንዲሁም የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ልዑክ ኤሌኖር ካሮይት በበኩላቸው፥ ስምምነቱ የአውሮፓ ህብረት እና የኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የቆየውን አጋርነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ስምምነቱ በጋራ መከባበር፣በጋራ እሴቶች እና ዘላቂ እድገት ላይ ለተመሠረተው አጋርነት ምስክር እንደሆነ ገልጸው፥ የኢኮኖሚ ትብብሩም ከኢትዮጵያ የሪሮርም አጀንዳ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ በበኩላቸው ፥ኢትዮጵያ አዳዲስ የኢንቨስትመንት እድሎችን ክፍት ለማድረግ እና ያላትን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የኢኮኖሚ ኢንቨስትመንት ትብብር አሁን ላይ ከ600 ሚሊየን ዩሮ በላይ የደረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ300 ሚሊየን ዩሮ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያን የኃይል መሠረተ ልማት ለማስፋፋት እና ለማዘመን የሚውል ነው።