ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት


48ኛው የአፍሪካ ሕብረት ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ዛሬ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተጀምሯል።

ስብስባው “ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ይደረጋል።

የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በሕብረቱ አባል አገራት የጋራ ፍላጎት የሆኑ የፖሊሲ ጉዳዮችን የሚያስተባብርና ውሳኔ የሚሰጥ ነው።

ምክር ቤቱ የሚቀርቡለትን የተለያዩ ጉዳዮች የሚመለከት ሲሆን በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተቀረጹ ፖሊሲዎች ትግበራ ላይ ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋል።

ምክር ቤቱ የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት መንግስታት የተሰየሙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም ሌሎች ሚኒስትሮች ጨምሮ ውሳኔ ሰጪ አካላትን የያዘ ነው።

የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የሚከተሉት ዋና ዋና ተግባራት አሉት

1. ለአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ አጃንዳዎችን ያዘጋጃል፤ ጉባኤው እንዲያጸድቃቸው ረቂቅ የውሳኔ ሀሳቦችን ያቀርባል።

2. የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አባላትን በመምረጥ የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ እንዲያጸድቅ ያደርጋል።

3. ምክር ቤቱ ከቀጠናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፤ ከሌሎች የአፍሪካ ተቋማትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚ ኮሚሽን ጋር ያለው ትብብርና ትስስር እንዲጠናከር የማስተዋወቅ ስራ ያከናውናል።

4. የአፍሪካ ሕብረትና የአፍሪካ አጋሮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ያዘጋጃል።

5. የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን መዋቅር፣ ተግባራትና መተዳደሪያ ሕጎች ላይ ምክረ ሀሳቦችን ለሕብረቱ መሪዎች ጉባኤ ያቀርባል።

6. በሁሉም የአፍሪካ ሕብረት መርሃ ግብሮች ላይ ጾታዊ እኩልነት መኖሩን ይከታተላል፣ ያረጋግጣል እንዲሁም እንዲኖር የማድረግ ስራዎችን ያከናውናል።

የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ውሳኔዎችን በስምምነት የሚያስተላልፍ ሲሆን፤ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ግን በሕብረቱ አባል አገራት ሁለት ሶስተኛ ድምጽ ውሳኔዎችን ያሳልፋል።

የምክር ቤቱ ስብስባን ለማካሄድ ከአፍሪካ ሕብረት አባልት አገራት ሁለት ሶስተኛው መሟላት አለባቸው።

በአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የሚቀርቡ አጀንዳዎች ለውይይት እንዲቀርቡ የምክር ቤቱ አባላት የአብላጫ ድምጽ ይሁንታ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር አንጎላ ስትሆን የሕብረቱ የወቅቱ ሊቀመንበርም ናት።

የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት አንድ አባል አገር ከሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ውጪ ስብስባ እንዲደረግ የቀረበለትን ጥያቄ ቢቀበል አዘጋጅ አገር (ኢትዮጵያ) ምክር ቤቱን በጋራ ሊቀመንበርነት የመምራት መብት አላት።

ምክር ቤቱ ስልጣንና ተግባሩን ለአፍሪካ ሕብረት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴና ልዩ ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴዎች በውክልና ሊሰጥ ይችላል።

የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ በዓመት ሁለት ጊዜ ሊሰበሰብ ይችላል፤ የምክር ቤቱ ስብስባዎች የሚካሄዱት የሕብረቱ መሪዎች ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት ነው።

ምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብስባ የምክር ቤቱ ሊቀመንበር፣ የአፍሪካ ሕብረት አባል አገርና የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ጥያቄ በማቅረብ ከአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ጋር ምክክር በማድረግና በአባል አገራቱ ሁለት ሶስተኛ ድምጽ ይሁንታ ማካሄድ ይችላል።

ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምጽ ለሕዝብ ክፍት ይሁን ብሎ እስካልወሰነ በስተቀር አስቸኳይ ስብስባውን በዝግ ያደርጋል።

የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በስሩ በእጩዎች፣ የአፍሪካ ሕብረት ስምምነቶች ትግበራ ላይ የሕብረቱ የበጀት ጉዳዮችና በአጀንዳ 2063 አፈጻጸም ላይ የሚሰሩ ንዑሳን ኮሚቴዎች አሉት።

48ኛው የአፍሪካ ሕብረት ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ እስከ ነገ ይቆያል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም