ቀጥታ፡

በአፍሪካ ችግር ፈች የምርምር ውጤቶችን ለማውጣት በሀገራት መካከል ትብብርና ቅንጅት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ችግር ፈች የምርምር ውጤቶችን ለማውጣት በሀገራት መካከል ትብብርና ቅንጅት ያስፈልጋል ሲሉ የምርምር ተቋማት ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች ገለጹ፡፡

የአፍሪካ ሕብረት ልማት ኤጀንሲ /AUDA-NEPAD/ ከአፍሪካ ሳይንስ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሳምንት 2026 "የአፍሪካን መጻኢ ዕድል በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን መበየን" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል፡፡


 

የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ባዮኢንፎርማቲክስ ኢንስቲትዩት የጤና መረጃ ሳይንስ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ኒኪ ቲፊን እንዳሉት፤ በአፍሪካ ችግር ፈች የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን ፈተናዎች ይበዛሉ፡፡

በአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ተመራማሪዎች በጤና፣ በድህነት ቅነሳና መሰል መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰሯቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች ተቀራራቢ ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ የጤና ዘርፍ ምርምርን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የቤተ ሙከራ ኬሚካል ግብዓትን ለማሳደግ የአምራች ኢንዱስትሪውን ማበረታታት ይገባል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የአስተሳሰብ አድማስን በማስፋት ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ወደ አፍሪካ ምድር እንዲመጡ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካ የካንሰር ምርምር ላይ የሚያተኩረው የየማቺ ባዮቴክኖሎጂ አንዱ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ያው ቤዲያኮ በአፍሪካ ብዙ ተመራማሪዎች የሎጂስቲክስና የአቅርቦት ሰንሰለት ችግር እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡


 

በአሕጉሪቱ ከምርምር ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ሀገራት መካከል ያለውን ትብብርና ቅንጅት ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ለምርምር ሥራዎች የሚያገለግሉ ግብዓቶችን እንቅስቃሴ በማሳለጥ የዘርፉ ውጤታማነት ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎ ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ አህጉራዊ አምራቾችን ማበረታታት ይገባልም ብለዋል፡፡


 

በኬንያ የናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተመራማሪ ቪንሰንት ኦኩንጉ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ በምርምር ተቋማት ያለው ቢሮክራሲ መስተካከል ያለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የምርምር ስራዎች ብክነትን የሚቀንሱ፣ የአፍሪካን ችግሮች የለዩና ትኩረታቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

ምርምር የምንሰራው የማህበረሰባችንን ችግር ለመፍታት ነው ያሉት ከፍተኛ ተመራማሪው፤ ምርምርን የቅንጦት ሥራ ማድረግ እንደማይገባም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም