የምስራቅ ዕዝ ለሀገሩ ዳር ድንበር ክብርና ሉአላዊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጀግንነት የቆመ ጠንካራ ሰራዊት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ ዕዝ ለሀገሩ ዳር ድንበር ክብርና ሉአላዊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጀግንነት የቆመ ጠንካራ ሰራዊት ነው
ጎዴ፤ የካቲት 4/2018 (ኢዜአ):- የምስራቅ ዕዝ ለሀገሩ ዳርድንበር ክብርና ሉአላዊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጀግንነት የቆመ ጠንካራ ሰራዊት ነው ሲሉ የእዙ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ፍቃዱ ፀጋዬ ገለጹ።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ፍቃዱ ፀጋዬ በኢትዮ-ሶማሊያ ድንበር ላይ ጥበቃና ስልጠና ላይ የሚገኙ የሰራዊቱን አባላት በመጎብኘት አነጋግረዋል።
የሰራዊቱ ዝግጁነት በሁሉም ረገድ ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ያነሱት ሜጀር ጄነራሉ ለየትኛውም ተልእኮና ግዳጅ አስተማማኝ ሰራዊት ተገንብቷል ብለዋል።
በዚህ ረገድ የምስራቅ እዝ በተልእኮና የግዳጅ አፈፃፀም የተሳኩ ተግባራትን እየፈፀመ መሆኑን አንስተው ሰራዊቱ የሀገሩን ክብርና ዳር ድንበር በአስተማማኝ መልኩ በማስጠበቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰራዊቱ ስልጠና እና ዝግጁነት የአሻባሪዎችና የጠላትን ፍላጎት በሩቅ ለማስቀረት እና ለማምከን መሆኑን አንስተው በዚህ ረገድ እዙ በላቀ ዝግጁነት ላይ ይገኛል ብለዋል።
የምስራቅ ዕዝ ለሀገሩ ዳርድንበር ክብርና ሉአላዊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጀግንነት የቆመ ጠንካራ ሰራዊት መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በዕዙ የኮር አዛዥ የሆኑት ብርጋዴር ጄነራል ፈይሳ አየለ፤ የሰራዊቱ አባላትና አመራሮች በየትኛውም ሁኔታ የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ሉአላዊነቷን ለማስጠበቅ ዝግጁ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።
የቀደምት አባቶችና አያቶችን ታሪክ አስቀጥሎ ለመሄድ ራሱን ባልተቋረጠና ውጤታማ በሆነ ስልጠና በመገንባት በየትኛውም አካባቢ ሊሰጥ የሚችል አገራዊ ተልዕኮ በብቃት መፈፀም የሚያስችል ቁመና ተገንብቷል ሲሉም አረጋግጠዋል።