የአፍሪካን የመሠረተ ልማት ጉድለት ለመሙላት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተምሳሌታዊ የልማት ስኬት ነው - የአፍሪካ ሕብረት የመሠረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን የመሠረተ ልማት ጉድለት ለመሙላት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተምሳሌታዊ የልማት ስኬት ነው - የአፍሪካ ሕብረት የመሠረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካን የመሠረተ ልማት ጉድለት ለመሙላት በራስ አቅም የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተምሳሌታዊ የልማት ስኬት መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት የመሠረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር ሌራቶ ማታቦጅ ገለጹ።
የሕብረቱ የመሠረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር ሌራቶ ማታቦጅ የአጀንዳ 2063ን የመሠረተ ልማት ግቦች ማፋጠን፣ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የአፍሪካ መሠረተ ልማት ፕሮግራም (PIDA) አፈጻጸምን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የገንዘብ (ካፒታል) ዋጋ እጅግ እየናረ መምጣቱን ኮሚሽነሯ ጠቁመዋል።
ይህ የካፒታል ውድነት በተለይ ለአፍሪካ አህጉር የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በፋይናንስ ለመደገፍ ትልቅ ፈተና እየሆነባት እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ለአህጉሪቱ ልማት እንቅፋት እየሆነ እንደሚገኝም አንስተዋል።
ለዚህም ማሳያ እንዲሆን እ.ኤ.አ. በ2026 ብቻ የተከሰቱት ድርቅና ጎርፍ በአህጉሪቱ መሠረተ ልማትና ኢኮኖሚ ላይ እያደረሱ ያለውን ጫና ጠቅሰዋል።
አሁን ያለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ከዋና ዋና ማዕድናት ፍላጎት ባለፈ እንደ ውሃ ባሉ ወሳኝ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ እየተደራጀ መሆኑን ኮሚሽነሯ ገልፀዋል።
የ2026 የአፍሪካ ህብረት መሪ ቃል በውሃ እና ሳኒቴሽን ዙሪያ ላይ እንደሚያተኩር ገልፀው፣ ይህም ህብረቱ በሰፊው እየተወያየበት ያለ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ውሃ እና ሳኒቴሽን እንደ ተራ ማህበራዊ አገልግሎት ብቻ ሳይታዩ እንደ ቁልፍ የኢኮኖሚ መሰረተ ልማት የሚታዩ መሆናቸውን አስገንዝበዋል ።
በተለይም አህጉራዊ የኢንዱስትሪ ጉዞን ለማፋጠን፣ ፋብሪካዎችን በብቃት ለማንቀሳቀስ እና ጤናማ የስራ ኃይል ለመገንባት የንጹህ ውሃ አቅርቦት እና የሳኒቴሽን ስርዓት አስፈላጊነት የማይተካ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ አህጉር 300 ሚሊዮን ህዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንደማያገኝ እና 780 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በቂ የሳኒቴሽን አገልግሎት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
በአህጉሪቱ ያለውን የውሃ ኢንቨስትመንት ክፍተት ለመሙላት 30 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
ይህንንም ለመፍታት የተለያዩ ፕሮግራሞች ተቀርጸው ተግባራዊ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
ከዕቅድ አንጻር የረጅም ጊዜ ሂደትን የሚጠይቅ መሆኑንም ተናግረው፤ ለዚህም በአህጉሪቱ ያለውን የመሠረተ ልማት ጉድለት መሙላት እና ሀብትን ማሰባሰብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን በራስ አቅም መገንባቷ ለአፍሪካውያን ተምሳሌት የሚሆን ታላቅ ስኬት መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከተለያዩ የአገር ውስጥ ምንጮች ሀብት በማሰባሰብ የገነባችው መሰረተ ልማት በሌሎችም ሊቀሰም የሚገባው ነው ብለዋል።
የአገር ውስጥ ሀብት አሰባሰብ ዋናው ቁምነገርም ይኸው መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሯ፤ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሊተገብሩት የሚገባ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡