ባለስልጣኑ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን ለሚዘግቡ የውጭ ሀገራት ጋዜጠኞች የ24 ሰዓት የተሳለጠ አገልግሎት እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ባለስልጣኑ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤን ለሚዘግቡ የውጭ ሀገራት ጋዜጠኞች የ24 ሰዓት የተሳለጠ አገልግሎት እየሰጠ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦ 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን ለሚዘግቡ የውጭ ሀገራት ጋዜጠኞች የ24 ሰዓት የተሳለጠ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።
39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓትን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የህብረቱ ዋና መስሪያ ቤት ይካሄዳል።
ከአፍሪካ ህብረት ጉባኤ አስቀድሞም 48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ፤ በርካታ የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች ጉባኤውን ለመዘገብ ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ ይህንን ለማስተናገድ በአየር መንገድ፣ በአፍሪካ ህብረት የባጅ ማዕከል እና በቢሮ ደረጃ የ24 ሰዓት የተሳለጠ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ጉባኤውን ለመዘገብ እስከ አምስት መቶ የሚጠጉ የተለያዩ ሀገራት ጋዜጠኞች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ጠቅሰው፤ ጋዜጠኞች አገልግሎት በቀላሉ የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱን ተናግረዋል።
በርካታ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ለጉባኤው ሽፋን ለመስጠት ምዝገባ እያካሄዱ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከውጭና ከሀገር ውስጥ የተውጣጡ አንድ ሺህ የሚጠጉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ኹነቱን እንደሚዘግቡ ተናግረዋል፡፡
ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ለኢትዮጵያ ገጽታ ግንባታ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
ጋዜጠኞቹ በኢትዮጵያ መገኘት በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለውን ሁለንተናዊና ፈጣን ለውጥ በተግባር የሚመለከቱበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ፣ እንግዶች መዲናዋን እንዲጎበኙ ከማስቻሉም ባለፈ፣ ለሀገራዊ ገጽታ ግንባታና ለቱሪዝም ዘርፉ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል።