በዞኑ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተመለከተ
መቱ፣ የካቲት 4/2018 (ኢዜአ):-በኢሉ አባቦር ዞን ከለውጡ አመታት ወዲህ በኢንቨስትመንት መስክ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተመለከተ።
በኢሉአባቦር ዞን መቱ ከተማ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እየተመዘገበ የሚገኘውን ውጤት ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት ጉዳይ ላይ የሚመክር የመንግስትና የባለሀብቶች ፎረም ተካሒዷል።
የመድረኩ ተሳታፊ ባለሀብቶች በዞኑ ከለውጡ ወዲህ ለኢንቨስትመንት መስኩ እየተሰጠ በሚገኘው ትኩረት ተሳትፏቸው እየጨመረ መሆኑን አንስተዋል።
ይሁንና በመሬት ማስተላለፍ፣ በመሠረተ ልማቶች ዝርጋታና በመሳሰሉት አሁንም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውን አመልክተዋል ።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢሉ አባቦር ዞን ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፀሐይ አክሊለ በተነሱ ሐሳቦች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በወረዳዎች የኢንቨስትመንት መሬትን ከማስተላለፍ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሩን ለመቅረፍ በየደረጃው የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን ጨምሮ እርምጃዎችን የመውሰድ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢንቨስትመንት መስኩ ተመዝግበውና ሂደቶችን ጨርሰው የመስሪያ ቦታ ወስደው ወደ ስራ መግባት ላይ መጓተት የሚያሳዩ ባለሀብቶችም በስምምነታቸው መሠረት ወደስራ መግባት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የኢሉ አባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በተለይ ለሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ችግሮችን መቅረፍ በሚገባቸው ሁኔታ ላይ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ለኢንቨስትመንት ቅበላ እንደመንገድ፣ ውሃ፣ ኤሌክትሪክና መንገድ ያሉ መሠረተ ልማቶችን የማሟላት በቂ ቅድመ ዝግጅቶች የበለጠ ትኩረት እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል።
በመስኩ የተሰማሩ ባለሀብቶችና ማሕበራትም በመስኩ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በዞኑ ያሉ አቅሞችን ከግንዛቤ ያስገባ፣ ምርትን መጨመር፣ በምርቶች ላይ እሴትን ጨምሮ ከማቅረብ፣ ጋር የሚያያዙና በተለይ በግብርናው ዘርፍ በመንግሥት የተቀረጹ ኢኒሼቲቮችን ታሳቢ ባደረጉ መስኮች ላይ አስፍተው እንዲመለከቱ አስገንዝበዋል።