ቀጥታ፡

በግብርናው ዘርፍ ዕሴት በመጨመር የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል የተጀመሩ ተግባራት ውጤታማ ናቸው

ሆሳዕና ፤ የካቲት 4/2018 (ኢዜአ) :- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በግብርናው ዘርፍ ዕሴት በመጨመር የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል የተጀመሩ ተግባራት  ውጤታማ መሆናቸው ተመላከተ፡፡

በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በከምባታና በስልጤ ዞኖች በእንስሳት ሀብት ልማት ማጠናከሪያ ፕሮግራም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ላይ የመስክ ምልከታ ተካሄዷል፡፡


 

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ አህመድ ሀቢብ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የተያዙ የልማት እቅዶችን ተግባራዊ በማድረግና ዕሴት በመጨመር የህዝብን ኑሮ የሚያሻሽል ተጨባጭ ውጤት ማስመዘግብ ተችሏል፡፡

በዚህም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና የገቢ አቅምን የሚያሻሽሉ ተግባራትን በተሻለ ደረጃ ከማከናወን ባለፈ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ በሰብል ልማት መስክ የተከናወኑት ተግባራት ለራስ ፍጆታና ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን ምርት የማምረት አቅምን ጨምሯል ብለዋል፡፡

ለአብነትም የወተት ምርታማነትን በማሳደግና ዕሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ገቢን የማሳደግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።


 

በግብርና ሚኒስቴር የአለም ባንክ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ፕሮጀክት ብሄራዊ አስተባባሪ ቶማስ ቸርነት (ዶ/ር) ፕሮጀክቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በወተት፤ በዶሮ በዓሳና የስጋ ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰማሩ ዜጎችን በመደገፍ ውጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት ላይ በተካሔደው የመስክ ምልከታ ምርታማነትን በማሳደግ እሴት ጨምሮ ለገበያ ከማቅረብ አንፃር ስኬታማ መሆናቸውን ተመልክተናል ብለዋል ፡፡ 


 

የከምባታ ዞን የጸዳል ህብረት ስራ ዩኒየን አስተባባሪ አቶ ደሳለኝ ደስታ በበኩላቸው እንዳሉት የሀምበሪቾ ወተት ማቀነባበሪያ ቀደም ሲል ጥሬና አሴት ያልተጨመረበት የወተት ምርት ለአካባቢው ህብረተሰብ ያቀርብ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለዩኒየኑ ባደረገው የወተት ማቀነባበሪያ ማሽን ድጋፍ በመታገዝ በወተት ምርት ላይ ዕሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ ማህበሩ ተጠቃሚ እየሆነ ነው ብለዋል፡፡

ዩኒየኑ በዶሮ እርባታ ዘርፍ ተሰማርቶ የእንቁላል ምርትን ለገበያ እንደሚያቀርብ የገለፁት ደግሞ በስልጤ ዞን የሚገኘው መሊቅ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልዳይም መሀመድ ናቸው፡፡ 


 

ዩኒየኑ ለሌሎች ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ስለመቻሉ  ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ 

በመስክ ምልከታ መርሐ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮችና የአለም ባንክ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም