ቀጥታ፡

በጎንደር ሰላምን በማጽናት የልማት ፕሮጀክቶች እንዲፋጠኑ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፏቸውን ያጠናክራሉ

ጎንደር፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፡-በጎንደር ከተማ ዘላቂ ሰላምን በማጽናት የልማት ፕሮጀክቶች እንዲፋጠኑ ተሳትፏቸውን የበለጠ እንደሚያጠናክሩ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

የከተማ አስተዳደሩ በወቅታዊ የሰላምና የልማት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሕዝባዊ የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

በመድረኩ የታደሙት የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የከተማዋ ሰላም የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል።

የሃይማኖት አባት መላከ ገነት አያሌው በየትኛውም እምነት የሰላም ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸው፣ ዜጎች ለሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና እንዲያጠናክሩ በየእምነት ተቋማቱ ትምህርት ይሰጣል ብለዋል።

በከተማዋ የመጣውን ሰላም በማጽናት የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲፋጠኑ የሃይማኖት አባቶች ሚናቸውን እንደሚያጠናክሩ አመልክተዋል።

የሀገር ሽማግሌ ሰለሞን ሞገስ እንደሚሉት፣ በከተማዋ እየታዩ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የሕብረተሰቡን ተስፋ የፈነጠቁና የመንግስት ቁርጠኝነት ማሳያ ናቸው።

የልማት ፕሮጀክቶቹ እንዲፋጠኑና ቀጣይነት እንዲኖራቸው የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን ማጽናት ላይ የድርሻቸውን ይወጣሉ ብለዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ለከተማዋ ዘላቂ ሰላምና ለልማት ፕሮጀክቶች ቀጣይነት የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች  ወሳኝ አበርክቶ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት የማይፈልጉ የሀገር ውስጥና የውጭ ሃይሎችን በጋራ ለመመከት አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል።

አለመግባባቶችን በውይይት ብቻ በመፍታት ሁሉም ዜጋ ሀገረ-መንግስት ግንባታው ላይ የድርሻውን እንዲወጣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የበለጠ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም