ቀጥታ፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ከ2 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል

ጭሮ፤ የካቲት 4/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት ከ2 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ  የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ተወካይ አቶ ጀማል ቃሲም ለኢዜአ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ 9 ሺህ ቶን ቡና ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

ባለፉት ስድስት ወራትም 2 ሺህ 100 ቶን ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ነው የገለጹት።

የቡና ምርቱ  በዞኑ 15 ወረዳዎች በሚገኙ 135 ህጋዊ ቡና አቅራቢ ነጋዴዎች አማካኝነት የቀረበ መሆኑን አመልክተዋል።

በግማሽ በጀት ዓመቱ ለማእከላዊ ገበያ የቀረበው የቡና ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር  ከ200 ቶን በለይ እድገት ማሳየቱን  ተናግረዋል።

በዞኑ በየዓመቱ በቡና የሚሸፈነው መሬት መጠን እና ምርታማነት እየጨመረ በመምጣቱ ብዛትና ጥራት ላይ በመስራት የተሻለ ምርት ለማቅረብ እንዳስቻለም ገልጸዋል።

ለአርሶ አደሮች የሚደረገው የቅርብ ድጋፍና ክትትል  የምርት ብክነትን እንዲከላከሉና ጥራት ላይ እንዲያተኩሩ ግንዛቤ የማስፋት ስራ መሰራቱም ወደ ማእከላዊ ገበያ የሚላከው ምርት እንዲጨምር አድርጓል ነው ያሉት።

በዞኑ  የተለያዩ አካባቢዎች  35 የደረቅ ቡና መፈልፈያ እንደስትሪዎች መኖራቸውም ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት ለማቅረብ  ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን  ገልጸዋል።

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት  ፅህፈት ቤት የቡናና ቅመማ ቅመም ልማት ቡድን መሪ አቶ ኦሉማ በዳኔ፤ በዞኑ ከ120 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተክል መሸፈኑን ገልጸዋል።

በልማቱ ከ230 ሺህ  በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ መቻላቸውን አብራርተው በዞኑ የቡና ልማት ስራን ለማስፋፋት በተከናወኑት ተግባራት  በመጪው ክረምት የሚተከሉ  ከ41 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞችን የማፍላት ስራ እየተከናወነ  እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅትም አርሶ አደሩ ከቡና ልማቱ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝም ከችግኝ ተከላ ጀምሮ እሰከ ቡና ግብይት ድረስ   መከተል በሚገባቸው ተግባራት ላይ ባለሙያዎች የቴክኒክ  ድጋፍና ክትትል እየተደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።

የቦኬ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ፅህፈት ቤት ሀላፊ  አቶ ሙዘይን አብደላ  በበኩላቸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በወረዳው የቡና ምርትማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ናቸው ብለዋል።

በተለይ በወረዳው የሚገኙ አርሶ አደሮች የጫት መሬትን በቡና ችግኝ እንዲተኩ በመደረጉ በዘርፉ ውጤት ለመመዝገቡ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው የተናገሩት። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም