ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሕብረትን ተቋማዊ ውጤታማነት ለማሳደግ ከአጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣሙ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት አንድ ዓመት የአፍሪካ ሕብረትን ተቋማዊ ውጤታማነት ለማሳደግ ከአጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣሙ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የአንጎላ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ሰብሳቢ አምባሳደር ቴቴ አንቶኒዮ ገለጹ። 

48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በሕብረቱ ዋና መስሪያ ቤት አዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ እና የአባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተገኝተዋል።

የአንጎላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ሰብሳቢ አምባሳደር ቴቴ አንቶኒዮ በዚሁ ወቅት፣ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ በአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ መዋቅር ውስጥ ስልታዊ ቦታ እንዳለው ገልጸዋል።

በአህጉራዊ ፖሊሲዎች መካከል ቅንጅት እንዲኖርና የጋራ አቋም እንዲያዝ የሚያደርገው ምክር ቤቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአፍሪካ ህብረት መንግስታት መዋቅራዊ ውሳኔዎችን ያዘጋጃል ብለዋል፡፡

ይህም ለሕብረቱ ተአማኒነት እና ውጤታማነት ወሳኝ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

የአንጎላ መንግስት ምክር ቤቱን በመራበት የስልጣን ዘመን ሁሉንም ያካተተ እና በውጤት ላይ ያተኮረ አካሄድ መከተሉን ተናግረው በዚህም በሁሉም አባል ሀገራት ድጋፍ እና ቁርጠኝነት ግቦቹን በስኬት ማጠናቀቁን ነው የገለፁት።

አሁንም ያልተጠናቀቁ ጉዳዮችን በኃላፊነት ስሜት ለመቋጨት እና ለቀጣዩ የጋራ ስራ ምዕራፍ የሚሆኑ ማሻሻያዎችን ለመጀመር በቆራጥነት መገኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አስፈጻሚው በቆይታው አስተማማኝ መሻሻሎችን ማስመዝገቡን አንስተዋል።

የአፍሪካ ሕብረትን ተቋማዊ ውጤታማነት ለማሳደግ ከአጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣሙ አሰራሮች ተግባራዊ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡  

እነዚህም ይበልጥ ሊገመቱ የሚችሉ እና የምንመኛት አፍሪካን ለመገንባት ከአጀንዳ 2063 ግቦች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም