መሰረተ ልማቷን በማፋጠን የቱሪዝም መዳረሻነቷ እየሰፋ የመጣችው ከተማ - ሐይቅ - ኢዜአ አማርኛ
መሰረተ ልማቷን በማፋጠን የቱሪዝም መዳረሻነቷ እየሰፋ የመጣችው ከተማ - ሐይቅ
ሐይቅ ፤የካቲት 4/2018 (ኢዜአ)፡-የሐይቅ ከተማ መሰረተ ልማቷን በማፋጠን የቱሪዝም መዳረሻነቷን እያሰፋች ትገኛለች።
የ''ገበታ ለትውልድ'' ፍሬ የሆነው ግዙፉ ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የ"ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክቶች ዋነኛ ዓላማ እንደ ሐይቅ ያሉ የታሪክ እና የገዳማት መገኛዎችን ለዓለም ገልጦ ማሳየት መሆኑን ተናግረዋል።
ሪዞርቱ የምድርን ተፈጥሯዊ ፀጋ ወደኢኮኖሚ ሞተርነት የቀየረ የልማት አሻራ መሆኑንም ነው ያነሱት።
በከተማዋ ያሉ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦችን የበለጠ ለማስተዋወቅ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እየተከናወኑ ነው።
እነዚህ መሰረተ ልማቶች የሐይቅ ከተማ የቱሪዝም መዳረሻነቷን የበለጠ በማስፋት የከተማዋን ነዋሪዎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው።
በአሁኑ ወቅትም በከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተፋጠነ ሲሆን የአስፓልት ንጣፍ ሥራውም ዛሬ ተጀምሯል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ መኮንን የዞኑን ሰላም በማጽናት የቱሪዝም እንቅስቃሴውን የሚያፋጥኑ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በአካባቢው የሚከናወኑ ልማቶች ለኑሮ፣ ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ መሆኑንም አንስተዋል።
የገበታ ለትውልድ አካል የሆነው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርትም ለአካባቢው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ተጨማሪ አቅም የፈጠረና የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደረገ ነው ብለዋል።
ሪዞርቱ ዓለምአቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባ በመሆኑ በክልሉ ብሎም በዞኑ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመጎብኘት የሚመጡ እንግዶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ያስችላል ብለዋል።
በሐይቅ ከተማዋ ዘላቂ ሰላም በማስፈን የቱሪዝም መዳረሻነቷን የሚያሰፉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው መሆኑን የገለጹት ደግሞ የከተማ ስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ከድር መሀመድ ናቸው።
በከተማዋ የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻልና አስፈላጊውን መሰረተ ልማት በማሟላት የጉብኚዎችን ቆይታ ጊዜ የሚያራዝሙ ሥራዎች እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም ሀብት ባለቤት ለሆነችው ሐይቅ ከተማ ተጨማሪ መዳረሻ በመሆን ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አመልክተዋል።