ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ነባር ችግሮችን ለመፍታትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ነባር ችግሮችን ለመፍታትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑን ሲቪክ ማህበራት ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ ምክክር ልብን ያሳርፋል፤ ውይይትም ስብራትን ይጠግናል ሲሉ የምክክርን ፋይዳ አስረድተዋል።

የአሁኑ ትውልድም ቅድመ አያቶቹ ለሀገር ሉዓላዊ አንድነት የከፈሉትን የጀግንነት ወኔ በመላበስ፣ በሰለጠነ የምክክር አውድ የተሰራች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

ኮሚሽኑ እስካሁን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ማወያየቱን ጠቅሰው፤ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአፍሪካ እና በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ኢትዮጵያውያንን ተደራሽ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በርካታ አጀንዳዎችን መሰብሰቡን ገልጸው፣ እስካሁን የአጀንዳ ማሰባሰብና በዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን የመለየት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው ሲቪክ ማህበራት እንዳሉት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ፕሬዚዳንት ሳባ ገብረመድህን እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የሴት ማህበራትን ያቀፈ አንድ ጥምረት በመመስረት ተሳትፏቸውን የሚያጠናክሩ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በእስካሁኑ የኮሚሽኑ ሂደት ጠንካራ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልፀው፣ በተለይም የሴቶች ድምጽ ለሀገራዊ ምክክር በሚል ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበት የሃገራዊ ምክክር መድረኮች መካሄዳቸውን አንስተዋል። 

በእነዚህ መድረኮች ላይ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ቢካተቱ ያሉዋቸውን አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ለብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ዳይሬክተር ገነት ስዩም በበኩላቸው፤ፈዴሬሽኑ በክልሎች ከወረዳ ጀምሮ የሴት አደረጃጀቶች ላይ ስለሀገራዊ ምክክር አስፈላጊነት እና ምንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በስፋት መስራታቸውን አብራርተዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፤ ምክክሩ በተለይ  የሃሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች ለማረቅ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝነት ያለው በመሆኑ የድርሻችንን ለማበርከት እንሰራለን ብለዋል።

በዋናው የሀገራዊ ምክክር መድረክ ላይ  ሴቶች በበቂ መጠን እንዲሳተፉ የሚያስችል ስራ መከናወኑንም  ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም