ቀጥታ፡

የአፍሪካን የተፈጥሮ ሃብት የዕሴት ሰንሰለት በማሻሻል የአህጉሪቷን የኢኮኖሚ ዕድገት ማፋጠን ያስፈልጋል -  ክላቨር ጋቴቴ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦የአፍሪካን የተፈጥሮ ሃብት የዕሴት ሰንሰለት በማሻሻል የአህጉሪቷን የኢኮኖሚ ዕድገት ማፋጠን እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀኃፊ ክላቨር ጋቴቴ አሳሰቡ፡፡

48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ’’ዘላቂ የውሃ ኑረትና ንጽህና ስርዓት፤ ለአጀንዳ 2063 ስኬት” በሚል መሪ ሃሳብ በሕብረቱ ዋና መስሪያ ቤት አዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በስብሰባው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የአንጎላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ ሊቀመንበር አምባሳደር ቴቴ አንቶኒዮ እና የአባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተገኝተዋል።

በዚሁ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸኃፊ ክላቨር ጋቴቴ፤ የሕብረቱ የውሃ አቅርቦትና ንጽሕና አጠባበቅ መሪ ሃሳብ ለአጀንዳ-2063 ስኬት ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

የአፍሪካን ዕምቅ የመሬት፣ የታዳሽ ኃይል፣ የማዕድንና የተፈጥሮ ሃብት ጸጋዎች እሴት ሰንሰለት በማሻሻል የአህጉሪቷን የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳለጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የአህጉሪቷ የብድርና የፊሲካል መዋቅራዊ ስብራቶችም ንግድና ኢንቨስትመንትን በማቀጨጭ በአፍሪካ ዕድገት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም የአፍሪካን የንግድና ኢንቨስትመንት በማሳደግ አስተማማኝ የኢኮኖሚ ምኅዳር ለመገንባት በአባል ሀገራት መካከል በጠንካራ ትስስር የተመሰረተ ትብብርን ማጠናከር እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

በቀጣይም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማቶችን በማስፋት አፍሪካዊያን የሚያጋጥማቸውን የውሃ ወለድ በሽታ ሥርጭት መግታት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።


 

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነት ሙሉ ትግበራን በማፋጠን የአህጉሪቷን ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም