በቴክኖሎጂ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የነገ ትውልድን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በቴክኖሎጂ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የነገ ትውልድን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ ናቸው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የነገ ትውልድን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ መሆናቸውን የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ቴክኖሎጂ ከአምሥቱ ብዝኃ ዘርፎች አንዱ የሆነው ነገ ለትውልድ ካለው ፋይዳ አንጻር መሆኑን መግለፃቸው ይታወቃል።
በቴክኖሎጂ ዘርፍ ከተከናወኑ ተግባራት አንዱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት(ኤአይ) መሆኑን ጠቅሰው፤ ከስድስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በማቋቋም ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል ገደማ እየገነባች ያለችው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ እየተጠናቀቀ መሆኑንና እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ሥራ እንደሚጀምር አመላክተዋል።
ከዛሬ 10 ዓመት ገደማ ጀምሮ ዓለም ለሥራ ከሚፈልጋቸው ሰዎች መካከል ከሞላ ጎደል 50 በመቶው የሚገኘው አፍሪካ ውስጥ እንደሚሆንና ይህንን በመረዳት ወጣቱን ለነገ ውድድር ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን እንዳሉት በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ወጣቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችሉ ናቸው።
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሀይፐርፎርማንስ ኮምፒውቲንግና ግዙፍ ዳታ ትንታኔ ልህቀት ማዕከል ኃላፊ ዮዲት ገብረኃላፍ እንዳሉት ቴክኖሎጂ በተለይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ውስን ሀብት ላለባቸው ሀገራት መፍትሄ ይዞ መጥቷል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት የህክምናና ግብርና ስራንና ብሎም የትምህርት ስርዓቱን ማዘመን የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ ብሎም ለአቅም ግንባታ ካለው ጠቀሜታ ባለፈ ለስራ እድል ፈጠራም ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ የተለያዩ አመርቂ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተው፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም ዲጂታላይዜሽንን የሚያፋጥኑ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና ሮቦቲክስ ልህቀት ማዕከል ኃላፊ ሀቢብ መሀመድ(ዶ/ር) በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ ለዲጂታላይዜሽን መስፋፋት መሰረት የሚጥሉ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
አካታች የፋይናንስ ስርዓት መፍጠር የሚያስችሉና የዲጂታል ክህሎትን የሚያሳድጉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀው ይህም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
ምሁራኑ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን አስፈላጊ ክህሎትና እውቀት መያዝ እንደሚገባ አንስተው፤ ተቋማትም የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት በሚያስችል አግባብ መደራጀት አለባቸው ብለዋል።