ቀጥታ፡

ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት የሚደረገው ጥረት የዜጎችን ርብርብ ይጠይቃል-ቀሲስ ታጋይ ታደለ 

ሆሳዕና፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት የሚደረገው ጥረት የዜጎችን ርብርብ እንደሚጠይቅ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ፡፡ 

የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ያዘጋጀው 6ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ "ሀይማኖት ለሰላም፣ ለአንድነትና ለአብሮነት" በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡


 

የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዚህ ወቅት፤ የሁሉ ነገር መሰረት የሆነውን ሰላምን በዘላቂነት ለማጽናት የዜጎች ርብርብ ወሳኝ መሆኑን  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዛሬው መድረክም  ሰላምን ለማዝለቅና  አብሮነትን ለማጠናከር እንዲሁም ልዩነቶችን በማጥበብ በአንድነት ለመጓዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የጠቆሙት፡፡

በሀይማኖት ተቋማትና በህዝቦች መካከል የኖረውን የአብሮነት እሴት ለመሸርሸር ተግተው የሚሰሩ ሀሰተኛ ማህበራዊ ገፆች እየበዙ መምጣታቸውን አስታውሰው፣ የእነዚህን አካላት የጥፋት ተግባር በቅንጅት ማክሸፍ ይገባል ብለዋል።

በተለይ የሀይማኖት ተቋማት ወጣቱንና ተከታዮቻቸውን ስለሰላም አበክረው ከማስተማር ባለፈ በተሳሳቱ መረጃዎች እንዳይታለሉ በማስገንዘብ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢና የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከፄዴቅ በበኩላቸው፣ ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናትና በህዝቦች መካከል የአብሮነት እሴትን ለማጠናከር የሀይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የሀይማኖት፣ የአመለካከትና የቋንቋ ልዩነቶች ቢኖርም የሁሉም የሃይማኖት ተቋማት አስተምህሮ በሰላም፣ በአብሮነትና በመከባበር መኖርን ያስተምራል ብለዋል።

ሰላሟ የተረጋገጠና የበለፀገች ሀገርን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ የአሁኑ ትውልድ ለሰላምና አብሮነት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ፣ ሰላም ለሁሉ ነገር መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፣ በክልሉ የሰፈነውን ሰላም በዘላቂነት አስጠብቆ ለማስቀጠል ህብረተሰቡን ያሳተፉ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ሰላምን ማጽናት በክልሉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለሰላም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በኮንፈረንሱ ላይ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሰላም ሚኒስቴር ተወካይ እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችም በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም