የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለሕንድ ባለሃብቶች ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለሕንድ ባለሃብቶች ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለሕንድ ባለሃብቶች ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠሩን በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ገለጹ።
ሕንድ በአፍሪካ ያላትን ከ100 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚጠጋ ኢንቨስትመንት እ.አ.አ እስከ 2030 በእጥፍ በማሳደግ ከአህጉሪቷ ጋር ያላትን አጋርነት ለማሳደግ እየሰራች መሆኗን አስታውቀዋል።
አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በቀጣናዊና በአፍሪካ አህጉር ጉዳዮች ላይ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ሥርዓት ወሳኝ ሚና እየተወጣች ነው።
የኢትዮጵያ መልክዓምድራዊና ስትራቴጂካዊ መገኛ ስፍራም ለአፍሪካ የዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መግቢያ በርነት እንድታገለግል እያስቻላት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ሕንድ በአፍሪካ ሀገራት የሚኖራትን ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ትብብር ለማጠናከር ከፍተኛ እገዛ እያደረገላት መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገነባው የተመራጭነትና ተወዳዳሪነት አቅም የአፍሪካ ሀገራትን ዓለም አቀፍ ስትራቴጂክ ትስስር በማጠናከር አይነተኛ ሚና እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮ-ሕንድ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዘመናትን የተሻገረ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ጉብኝትም የሀገራቱን ግንኙነት ወደስትራቴጂክ አጋርነት ማላቅ አስችሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም የሕንድ ባለሃብቶችን የንግድና ኢንቨስትመንት ተሳትፎ በማሳደግ ምቹ የትብብር ምኅዳር መፍጠር እንዳስቻለ አስታውቀዋል።
የ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ዘላቂ " የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ ይታወቃል።
አምባሳደር አኒል፤ የሕብረቱ መሪ ሃሳብ በውሃ አቅርቦትና ንጽህና አጠባበቅ ዘርፍ አጀንዳ 2063ን ለማሳካት የተያዘውን ግብ ለማሳካት አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።
የአህጉሪቱን የድርቅ ተጋላጭነትና የውሃ ወለድ በሽታዎች ሥርጭት በመቀነስ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርታማነት ዘላቂ የውሃ ሃብት አቅም ለመገንባት ወሳኝ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ሕንድ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር ያላትን ስትራቴጂክ አጋርነት በማላቅ ለአጀንዳ-2063 ስኬት የምታደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
ሕንድና የአፍሪካ ሀገራት በግብርና፣ የምግብ ማቀነባበር፣ ማዕድን፣ ዲጂታል መሰረተ ልማትና በርካታ ዘርፎች በትብብር እየሰሩ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በዚህም ሕንድ በአፍሪካ ያላትን ከ100 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚጠጋ ንግድና ኢንቨስትመንት እ.አ.አ እስከ 2030 በእጥፍ በማሳደግ ከአህጉሪቷ ጋር ያላትን አጋርነት የበለጠ ለማስፋት እየሰራች መሆኗን አስታውቀዋል።