ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተመለከትነው ዕድገትና የከተሞች ልማት በቀጣናው መስፋት ያለበት ነው

ድሬዳዋ፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የተመለከቱት ዕድገትና የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በምሳሌነት የሚጠቀስና በቀጣናው መስፋት ያለበት መሆኑን የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ወጣቶች ገለፁ።


 

ከተለያዩ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የተውጣጡ ወጣቶች በድሬዳዋ ባካሄዱት ጉባኤ የቀጣናውን ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ለማስቀጠልና የአፍሪካ የልማት አጀንዳዎችን ለማሳካት ግንባር ቀደም ሚናቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በጉባኤው ላይ የተሳተፉት ወጣቶች በቆይታቸው የተመለከቱትን የኢትዮጵያ ልማትና ለውጥ አስመልክተው ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።


 

ከሱማሊያ የተሳተፈው ወጣት ሐሺም ፋራህ እንዳለው፤ መንግስትና ነዋሪዎች ተቀናጅተው እያከናወኑ የሚገኙት የልማት ስራ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተሞችን ውብ እና ማራኪ የመኖሪያና የስራ ማዕከል አድርጓቸዋል።

በተለይም አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ ደረጃዋን በሚመጥን መንገድና የከተማ ልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን በመግለፅ።

ባለፉት ጥቂት አመታት በኢትዮጵያ እየተመዘገበ የሚገኘው ለውጥ በግልጽ ያስተዋልነውና ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው ያለው ደግሞ ከደቡብ ሱዳን የተሳተፈው ወጣት ፔይ ጆ ሹዋ ነው።


 

በኢትዮጵያ የተመዘገበውን ዕድገትና ለውጥ በቀጣናውም ሆነ በመላው አፍሪካ ለማስፋት ጉባኤው ወሳኝ እንደነበር አንስቷል።


 

ከሱማሊያ ፑንትላንድ የተሳተፈው ወጣት መሐሙድ ኢድሪስና ከሶማሌላንድ የተሳተፈችው ወጣት ፈሪያ መሐመድ በበኩላቸው ወጣቶች ወደ መሪነት ከተሳቡና ዕድል ከተሰጣቸው በኢትዮጵያ እየተመዘገበ የሚገኘውን አይነት ለውጥና ዕድገት በቀጣናው ማስፋት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በአርአያነት የምንወሰደው የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና እያስመዘገቡ የሚገኙትን የሚታይ ለውጥ ነው ብለዋል።

ከጅቡቲ የተሳተፈው ወጣት አብዱልፈታህ ዮሱፍ በበኩሉ አፍሪካ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ እና ሚና በከፍታ ለማረጋገጥና አጀንዳ 2063ን ለማሳካት የአህጉሩ ወጣቶች ሚና የጎላ መሆኑን ተናግሯል።


 

የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በተቀናጀ መንገድ ተባብረውና ተደጋግፈው በመትጋት ከድህነት ለመውጣት ቆርጠው መነሳታቸውንም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም