ቀጥታ፡

ባለፉት ስድስት ወራት ከ220 ቶን በላይ የጎማ ዛፍ ጥሬ ምርት ተመርቷል

ሚዛን አማን፤ የካቲት 4/2018(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከ220 ቶን በላይ የጎማ ዛፍ ጥሬ ምርት ማምረቱን በኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የጎማ ዛፍ ተከላና ምርት ፕሮጀክት አስታወቀ።


 

በኮርፖሬሽኑ ጎማ ዛፍ ተከላና ምርት ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘማች ሳድንስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኮርፖሬሽኑ የጎማ ዛፍ ልማትን በማስፋፋት ለኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልገውን ጥሬ ምርት በሀገር ውስጥ አቅም ለመሸፈን እየሰራ  ነው።


 

ለዚህም  በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ  በ3ሺህ 884 ሄክታር መሬት  የጎማ ዛፍ  በማልማትና ጥሬ ምርቱ ላይ እሴት በመጨመር ለድርጅቶች በሽያጭ  እያቀረበ ነው።

የጎማ ዛፍ ልማቱን በማስፋት በበጀት ዓመቱ ከ220 ቶን በላይ ምርት በማምረት ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

የጎማ ልማትን ውጤታማነት ለማሳደግ ኮርፖሬሽኑ በኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦር ዞን 2500 ሄክታር የማስፋፊያ መሬት መረከቡን አንስተው፣ ለዚህም በመጪው ክረምት የሚተከሉ 82 ሺህ ችግኞችን እያፈሉ መሆናቸውን አክለዋል። 


 

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ የጎማ ልማት ሥራው ለኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልግ ጥሬ ምርት በሀገር ውስጥ ለማቅረብ ከማስቻሉ ባለፈ ከ560 ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስችሏል።

የጎማ ዛፍ ምርትን በሀገር ውስጥ ማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት በማስቀረት የውጭ ምንዛሬን የሚቀንስ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ አዲስ ብርሃን በተሰኘ የልማት ጣቢያ መለስተኛ ኢንዱስትሪ በመትከል ምርቱን በከፊል አቀናብሮ  ለገበያ እያቀረበ  መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በፕሮጀክቱ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል ወጣት ዳዊት አለማየሁ እና ወይዘሮ ዘውዲቱ ገብረ ማርያም  እንደገለጹት፤ የጎማ ዛፍ ወተትን የማርጋት፣ የማድረቅና ተያያዥ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ ይገኛሉ።


 

የምርት ዝግጅት ሂደቱ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ባገኙት የሙያ ስልጠናና ልምድ ታግዘው በመስራት ምርቱን ለሽያጭ የማዘጋጀት ሥራ እያከናወኑና ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም