ቀጥታ፡

48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2018 (ኢዜአ)፦ 48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ዛሬ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይጀመራል።

የአፍሪካ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ዲፕሎማቶችና የሕብረቱ ተቋማት አመራሮች ይሳተፋሉ።

በስብሰባው ላይ የሚሳተፉ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።

ምክር ቤቱ በጥር ወር 2018 ዓ.ም 51ኛው የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ በተወያየባቸው አጀንዳዎች ላይ ምክክር ያደርጋል።

የምክር ቤቱ ስብሰባ የአፍሪካ ሕብረት ተቋማትና አደረጃጀቶች፣በምክር ቤቱ ስር የሚገኙ ኮሚቴዎችና ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዲሁም የአጀንዳ 2063 የአፈጻጸም ሪፖርት ያዳምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የውሃ ደህንነት እና የንጽህና፣ አጠባበቅ፣ የአጀንዳ 2063 ትግበራን እና አህጉራዊ ትስስር፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ የሰው ኃይል ልማት፣ ተቋማዊ እና የፋይናንስ ሪፎርሞች፣ ቀጣናዊ አጋርነት እና አፍሪካ በዓለም መድረክ ያላት ሚና ጉባኤው ከሚመክርባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

አፍሪካ እ.አ.አ በ2025 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የነበራትን ተሳትፎም ይገመግማል።

ምክር ቤቱ በስብሰባው ምርጫዎችን በማካሄድ ለአፍሪካ ህብረት አደረጃጀቶች ውስጥ የሚሾሙ ሰዎችን ይመርጣል።

የአፍሪካ ህብረት ቁልፍ የሰው ሀብት ሪፎርም አካል የሆነው የክህሎት ኦዲቲ እና የብቃት መለኪያ ሂደት (SACA) ያለበት ደረጃ ላይ እንደሚወያይ ኢዜአ ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የህግ ማዕቀፎች እና የአስተዳደር ጉዳዮችም ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል።

የአፍሪካ ሕብረት ተቋማትና አደረጃጀቶች መግለጫዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶች ዛሬ ይካሄዳሉ።

የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚከናወነው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችንም ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የምክር ቤቱ መደበኛ ስብስባ እስከ ነገ ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም