ቀጥታ፡

ማንችስተር ዩናይትድ ከዌስትሃም ዩናይትድ ጋር አቻ ተለያየ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ጨዋታ ዌስትሃም ዩናይትድ እና ማንችስተር ዩናይትድ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል።

ማምሻውን በለንደን ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቶማስ ሶቼክ በ50ኛው ደቂቃ የዌስትሃም ዩናይትድን የመሪነት ግብ አስቆጥሯል።

ጨዋታው በዌስትሃም አሸናፊነት ተጠናቀቀ ሲባል ተቀይሮ የገባው ቤንጃሚን ሼስኮ በ96ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ግሩም ግብ ዩናይትድን አቻ አድርጓል።

ማንችስተር ዩናይትድ በጨዋታው ብልጫ ቢወስድም ግልጽ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ተቸግሯል።

ዌስትሃም ዩናይትድ በጥልቀት በመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ቢጫወትም ውጤቱን ማስጠበቅ አልቻለም።

ከአራት ተከታታይ ድሎች በኋላ አቻ የወጣው ማንችስተር ዩናይትድ በ45 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

ዩናይትድ ከሁለት ዓመታት በኋላ በሊጉ አምስት ተከታታይ ድል የማስመዝገብ ውጥን አልተሳካም።

ዌስትሃም ዩናይትድ በ24 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ዌስትሃም ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ነጥብ ጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም