ኢትዮጵያ ፀጋዎቿን ወደ ሀብት ለመቀየር የቀየሰቻቸው ስልቶች የበለፀገ ዜጋና ሀገር መገንባት እያስቻሉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ፀጋዎቿን ወደ ሀብት ለመቀየር የቀየሰቻቸው ስልቶች የበለፀገ ዜጋና ሀገር መገንባት እያስቻሉ ነው
አዲስ አበባ፤የካቲት 3/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ፀጋዎቿን ወደ ሀብት ለመቀየር የቀየሰቻቸው ስልቶች የበለፀገ ዜጋና ሀገር መገንባት እያስቻሉ መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የማኒፌስቶ እና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ይፋ ማድረጊያ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩም የፓርቲው የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመወዳደሪያ ምልክት የስንዴ ነዶ፤ የማኒፌስቶ መሪ መልዕክቱን ደግሞ "ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር!" በሚል ስያሜ ይፋ አድርጓል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት በስድስተኛው እና በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫዎች መካከል ፓርቲው እውን ያደረጋቸውን ሁለንተናዊ ስኬቶች በንፅፅር አቅርበዋል።
በዲጂታላይዜሽን የኢኮኖሚ ግንባታ፣ በክፍያና ግብይት፣ በዲጂታል ፋይናንስና መታወቂያ፣ በኢንተርኔት፣ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በዲጂታል ክህሎት እመርታዊ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በድካም ቀና ብለን ያጠናቀቅነው የትውልድ ፕሮጀክት ነው ያሉት አቶ ተመስገን፤ ብልፅግናን መምረጥ የዲጂታል ኢትዮጵያ ነጋችንን ብሩህ ማድረግ ነው ብለዋል።
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስኬቶችና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያ ጸጋዎቿን ወደ ሃብት የቀየረችበት ስልት ኢንዱስትሪያዊት ሀገር ለመፍጠር የተጀመረው ጉዞ የሰመረ መሆኑን እንደሚያመላክት ተናግረዋል።
በተጨማሪም በዲጂታላይዜሽንና በዘመናዊ የከተሜነት ምኅዳር አዳዲስ የለውጥ መንገዶች የተመዘገቡ ውጤቶች ኢትዮጵያዊያንን ቀና ያደረጉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
የብልፅግና መንግስት የወረሰው እጅ ከወርች የተቀፈደደና ከጠቅላላው ኢኮኖሚ 60 በመቶው ዕዳ የሆነበትን የኢኮኖሚ ሥርዓት መሆኑን አስታውሰው፤ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ከዕዳ ወደ ምንዳ የተሻገረ ዕድገት እየተገነባ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዓለም አቀፍ አድናቆትና ሀገራዊ ውጤት በማስገኘት የብልፅግናን ኢኮኖሚ ከአግላይ ከልካይ ወደ አስቻይ ምኅደር ተሸጋግሯል ብለዋል።
በግብርና መስክም በሰብልና በእንስሳት ሃብት ያልተነኩ ሀገራዊ ፀጋዎችን ዘመናዊ የምርታማነት አቅም በመገንባት ከአፍሪካ ቀዳሚ አምራች ሀገራት ተርታ የሚያሰልፍ ዕድገት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊንን አንገት ካስደፉ ጠባሳዎች አንዱ ፀጋችንን በመቅበር ድህነታችንን እያከበርን መቆየታችን ነው ያሉት አቶ ተመስገን፤ ኢትዮጵያ ከድህነት ጋር መነሳቷም ያስቆጫል ብለዋል።
ብልፅግናም ቁጭትን በፈጠራና ፍጥነት ወደ ተዓምር መቀየር መቻሉን በታሪክና ቅርስ ጥበቃ የቱሪዝም ልማት የተገነቡ አስደናቂ ልማት ታሪክን ወደ ሃብት፣ ቅርስን ወደ እሴት መቀየር እንደቻለ አንስተዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት፣ የብልፅግና ፓርቲ በኢንዱስትሪ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በከተማና ገጠር ኮሪደር፣ ጤና፣ ትምህርትና በተለያዩ መስኮች ኢትዮጵያን ጀምሮ መጨረስ መታወቂያዋ ማድረግ ያስቻሉ እመርታዊ ውጤቶች ማስመዝቡን አስታውቀዋል።
በመድረኩም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሀላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፤ የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት፤ የኢንስፔክሽንና የሥነምግባር ኮሚሽን አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።